በድሬዳዋ ገጠር ቀበሌ የተገነባ ጥልቅ የውሀ ጉድጓድ አገልግሎት መሰጠት ጀመረ

95
ኢዜአ ታህሳስ 03 / 2012 ዓ.ም በድሬዳዋ አስተዳደር በገጠር ቀበሌ ከ18 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የተገነባ ጥልቅ የውሀ ጉድጓድ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ። ጥልቅ የውሃ ጉድጓዱ የድሬዳዋ ገጠር ቀበሌዎች ድሬ -ጃራ-ሀረር የውሃ ፕሮጀክት አካል መሆኑ ተነግሯል ። የድሬዳዋ ግብርና፣ ውሃና ማዕድን ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ ለኢዜአ እንደገለጹት ጥልቅ ጉድጓዱ በተገነባበት አሰሊሶ ገጠር ቀበሌ ነዋሪዎችን የተቀናጀ የንፁህ መጠጥ ውሃና የመስኖ ልማት ተጠቃሚ የሚያደርገግ ነው። ጥልቅ ጉድጓዱ በሰኮንድ 65 ሌትር ውሃ  የማመንጨት አቅም እንዳለው ተናግረዋል ። የውሃ ተቋሙ የነዋሪዎቹን የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር ከመፍታት ባለፈ ለመስኖ አገልግሎት እንደሚውል ገለጸዋል ። እንደኃላፊው ገለጻ የውሃ ጉድጓዱ በዚህ ዓመት በቀበሌው 40 ሄክታር መሬት መስኖ ለማልማት የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካትም የሚያግዝ ነው። በአስተዳደሩ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የድሬዳዋ ንግድ፣ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ከድር ጁሃር የውሀ የቋሙ የነዋሪውን ጥያቄ ለመመለስ የተገነባ መሆኑን ተናግረዋል ። ህብረተሰቡ አገልግሎቱን ለማግኘት ላሳየው የረዥም ጊዜ ትዕግስት ምስጋናቸውንም አቅርበዋል። የቀበሌው ነዋሪ ወይዘሮ አሻ አህመድ በበኩላቸው የንፁህ መጠጥ ውሃ ፍለጋ በቀን ከሁለት ሰዓት በላይ በእግር ይጋዙ እንደነበር አስታውሰዋል ። በቀበሌው የተገነባው የውሃ ተቋም የነዋሪውን የመጠጥ ውሃ ችግር ከማቃለሉ በተጨማሪ የመስኖ ልማት ለማካሄድ እንደሚያገለግልም ተናግረዋል። "በአካባቢው ለም መሬት ቢኖርም የመስኖ ተጠቃሚ ሳንሆን ቆይተናል"ያሉት ደግሞ የቀበሌው ነዋሪ አርሶ አደር ያህያ መሐመድ ናቸው ። የውሃ ተቋሙ አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ልማቱን በማካሄድ ተጠቃሚ እዲሆኑ እድል እንደፈጠረላቸውም ገልጸዋል። ነዋሪዎቹ የውሀ ተቋሙ የረዥም ጊዜ ጥያቄያውን የመለሰ ስለመሆኑ በመግለፅ ምስጋናቸውን አቅርበዋል ።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም