ዩኤስአይዲ እና አዋሽ ባንክ በግብርና ለተሰማሩ የንግድ ድርጅቶች ብድር ለማመቻቸት የሚያስችል የትብብር ማዕቀፍ ይፋ አደረጉ

143
ኢዜአ ታህሳስ 3 ቀን 2012 ዓ.ም የአሜሪካ የልማት ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስአይዲ) እና የአዋሽ ባንክ በኢትዮጵያ በግብርና ለተሰማሩ የንግድ ድርጅቶች የብድር አቅርቦት ማመቻቸት የሚያስችል የ6 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዶላር አዲስ የትብብር ማዕቀፍ ዛሬ ይፋ አደረጉ። ዩኤስአይዲ የኢትዮጵያ ቢሮ ምክትል ዳይሬክተር ሚስ ሶኒላ ሀይሲ እና የአዋሽ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ፀሐይ ሽፈራው የትብብር ማዕቀፍ ስምምነቱን ተፈራርመዋል። በትብብር ማዕቀፉ መሰረት የብድር አቅርቦት እድሉን የሚያገኙት ለማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት እንዲሁም በግብርናው የተሰማ አነስተኛና መካከለኛ የንግድ ድርጅቶች እንደሆኑ በአዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል። በዩኤስአይዲ የልማት ብድር ባለስልጣን ስምምነት መሰረት ማዕቀፉ የኢትዮጵ ንግድ ባንክ የብድር አቅርቦት ተደራሽ ባልሆነባቸው አካባቢዎች የሚሰጠውን ብድር የሚሳድግ እንደሆነ ተገልጿል። ብድሩ ለአርሶ አደሮችና የግብርና የቢዝነስ ተቋማት የሚያስፈልገውን የግል ካፒታል ተደራሽ በማድረግ ምርታማነትን በማሳደግና ኢትዮጵያ የግብርና ዘርፉን ለማዘመን የምታደርገውን ጥረት ያግዛልም ተብሏል። የግል የካፒታል ምንጮች በክልሎች፣ በወረዳና በቀበሌ የሚገኙ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ለግለሰቦችና ለአነስተኛ የንግድ ስራዎች በተለይም አነስተኛ ማሳ ላላቸውን አርሶ አደሮችና ለምርታማ ሴፍቲኔት መርሃ  ግብር ተጠቃሚዎች የሚሰጠውን የብድር መጠን የማሳደግ አቅም እንዳላቸው መግለጫው ያመለክታል። በተጨማሪም ይህ የትብብር ማዕቀፍ አዋሽ ባንክ በግብርና ዘርፍ ለተሰማሩ አነስተኛና መካከለኛ የንግድ ድርጅቶች ቀጥታ ብድር መስጠት ያስችለዋል። በኢትዮጵያ 70 በመቶ የሚጠጋው የሰው ሃይል የተሰማራበት ለኢትዮጵያ አጠቃላይ የምርት መጠን 34 በመቶ አስተዋጽኦ እያደረገ ያለው የግብርናው ዘርፍ ያለው የብድር አቅርቦት ተደራሽነት ዝቅተኛ ነው። ዩኤስአይዲ የኢትዮጵያ ቢሮ ምክትል ዳይሬክተር ሚስ ሶኒላ ሀይሲ ''ለምንሰጠው ገንዘብ የተሻለ ውጤት ማግኘትን በምንገልጽበት ወቅት በኢትዮጵያ የግብርና ዘርፍ ላይ መዋዕለ ነዋይ ማፍሰስ ትክክለኛው አማራጭ እንደሆነ እንረዳለን'' ብለዋል። የትብብር ማዕቀፉ በአጠቃላይ የኢኮኖሚ እድገቱን እንዲፋጠን የሚያስችል እንዲሁም በተመሳሳይ አርሶ አደሮችና ቤተሰቦቻቸው ዘላቂነት ያለው ተጠቃሚነት እንዲኖራቸው እንደሚያደርግ ገልጸዋል። የአዋሽ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ፀሐይ ሽፈራው በበኩላቸው ከዩኤስአይዲ ትብብር ባንኩ ለግሉ ዘርፍ የማይክሮ ፋይናንስ እንዲሁም በግብርናው ዘርፍ ለተሰማሩ አነስተኛና መካከለኛ የንግድ ድርጅቶች የሚያበድረውን የገንዘብ አቅም እንደሚያሳድገው ተናግረዋል። መንግስት በግብርናው ዘርፍ ካስቀመጣቸው ዋና ስትራቴጂካዊ የትኩረት አቅጣጫዎችን መሰረት በማድረግ ባንኩ የግብርናውን ዘርፍ ለመደገፍ እየሰራ እንደሆነ ገልጸዋል። ባንኩ ግብርናን አስመልክቶ ለሚሰጣቸው ብድሮች ከፍተኛ የሆነ የወለድ መጠን ቅናሽ ማድረጉን በማሳያነት ጠቅሰዋል። ባንኩ በዩኤስአይዲ የልማት ፕሮጀክቶች ላይ በአጋርነት በመስራት ሙሉ ለሙሉ ብድር ተመላሽ በማድረግ ውጤታማ ተግባር ማከናወኑም ተመልክቷል። የአሜሪካ መንግስት ባለፉት አምስት ዓመታት በኢትዮጵያ ለልማትና ሰብአዊ እርዳታ አራት ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ድጋፍ ማድረጉን የኤምባሲው መግለጫ ያትታል።            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም