የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሦስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ይካሄዳሉ

85
ኢዜአ ታህሳስ 3 ቀን 2012 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሦስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ይካሄዳሉ። በነገው መርሃ ግብር ጅማ አባ ጅፋር ከሲዳማ ቡና ሊያደርገው የነበረው ጨዋታ ወደ እሁድ ተዛውሯል። ነገ በአዲስ አበባ ስታዲዮም ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ሰበታ ከተማ እና አዳማ ከተማ ጨዋታውን ያደርጋሉ። በክልል ከተሞች በዝዋይ ሼር ኢትዮጵያ ሜዳ ወልቂጤ ከተማ ከፋሲል ከነማ፣ በሶዶ ስታዲዮም ወላይታ ድቻ ከቅዱስ ጊዮርጊስ፣ በትግራይ ስታዲዮም ስሑል ሽረ ከሊጉ መሪ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርስቲ ሁሉም በተመሳሳይ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። በሀዋሳ ስታዲዮም ሀዋሳ ከተማ ከባህርዳር ከተማ እንዲሁም በድሬዳዋ ስታዲዮም ድሬዳዋ ከተማ ከሀዲያ ሆሳዕና በተመሳሳይ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። ነገ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት በጅማ ስታዲዮም ጅማ አባ ጅፋር ከሲዳማ ቡና ጨዋታቸውን ማድረግ የነበረባቸው ሲሆን ጅማ አባ ጅፋር ታህሳስ 1 ቀን 2012 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስታዲዮም ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ጨዋታ በማድረጉ ተራዝሞ እሁድ ዘጠኝ ሰዓት እንዲደረግ መወሰኑን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል። እሁድ የአምናው የፕሪሚየር ሊጉ አሸናፊ መቐለ ሰብዓ እንደርታ በትግራይ ስታዲዮም ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ኢትዮጵያ ቡናን ያስተናግዳል። ወልቂጤ ከተማ፣ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲና ስሑል ሽረ የእግር ኳስ ሜዳቸው በእድሳት ላይ የሚገኝ በመሆኑ ጨዋታቸውን በሌላ ሜዳ የሚያደርጉ ይሆናል። የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በስድስት ነጥብ ሲመራ፣ ፋሲል ከነማ፣ ሀዋሳ ከተማ፣ ባህርዳር ከተማ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስና አዳማ ከተማ በተመሳሳይ አራት ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው በቅደም ተከተል ከሁለተኛ እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል። በዘንድሮው የውድድር ዓመት ፕሪሚየር ሊጉን የተቀላቀሉት ሰበታ ከተማ፣ ወልቂጤ ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ ከ14ኛ እስከ 16ኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም