በኢትዮጵያ በመገናኛ ብዙሃን ዘርፍ ላይ የተሰማራው 'አፍሪ ሄልዝ ትሬዲንግ' አለም አቀፍ እውቅና ካላቸው ተቋማት ጋር ሊሰራ ነው

68
አዲስ አበባ ሰኔ 15/ 2010 በኢትዮጵያ በቅርቡ በመገናኛ ብዙሃን ዘርፍ ላይ የተሰማራው 'አፍሪ ሄልዝ ትሬዲንግ' አለም አቀፍ እውቅና ካላቸው አቺ ባደም ሆስፒታል ግሩፕና አሎሃ ሜዲካል ቱር ኤንድ ትራቭል ድርጅት ጋር ለመስራት ስምምነት ላይ መድረሱን አስታወቀ። አፍሪ ሄልዝ ትሬዲንግ በጤና ዘርፍ ላይ የሚሰራና በህክምና ባለሙያዎችና ባለሀብቶች የተቋቋመ ሲሆን በኢትዮጵያና በሌሎች አፍሪካ አገሮች ላይ የሬዲዮና የቴሌቭዥን ጣቢያዎች፣ የጥሪ ማዕከላትና የኦንላይን ሚዲያ አገልግሎት የሚሰጥ ተቋም ነው። የአፍሪ ሄልዝ ትሬዲንግ ቴሌቭዥን ጣቢያ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ሜሎኒ በቀለ እንደገለጹት፤ ተቋሙ በጤና ላይ ያተኮሩ ልዩ ዘገባዎችን የሚያቀርብ በአፍሪካ የመጀመሪያው የመገናኛ ብዙሃን ተቋም ለመሆን አደረጃጀትና መሳሪያዎችን እያሟላ ይገኛል። አቺ ባደም ሆስፒታል ግሩፕ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን የህክምና ባለሙያዎች በመያዝ በአለም አቀፍ ደረጃ ሁለተኛ መሆኑንና አሎሃ ሜዲካል ቱር ኤንድ ትራቭል በርካታ ዜጎች በውጭ አገሮች ህክምና እንዲያገኙ እድል መፍጠሩን ገልጸዋል። ተቋሙ ከነዚህ ዓለም ዓቀፍ ተቋማት ጋር መስራት በአገርና በአህጉር አቀፍ ደረጃ ለጤናው ዘርፍ ስኬት የሚያግዙ ስራዎች እንዲሰራ ለማድረግ የላቀ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ነው የተናገሩት። ከሌሎች አገር፣ አህጉርና አለም አቀፍ ተቋማት ጋር ለመስራት የሚያስችል ስምምነት ለማድረግ ተቋሙ ዝግጅቱን ማጠናቀቁንም ጠቁመዋል። ከድርጅቶቹ ጋር የተደረገው ስምምነት በተቋማቱ መካከል የህክምና ባለሙያዎች የልምድ ልውውጥና ስልጠና፣ የድርጅቶቹ ባለሙያዎች በተቋሙ ዘገባዎች ላይ በመገኘት ገለጻ እንዲሰጡ የሚያስችል መሆኑንም አብራርተዋል። በአቺ ባደም ሆስፒታል ግሩፕ የአለም አቀፍ የቢዝነስ ዴቨሎፕመንት ዳይሬክተር ሚስተር ኤልያስ ቤንቤንስኪ በበኩላቸው ''ድርጅቱ 27 አመታትን ያስቆጠረና በተለያዩ አገሮች የሚገኙ ሆስፒታሎች፣ የህሙማን ማቆያ ማዕከላትና በርካታ የህክምና ባለሙያዎችን አካቶ እየሰራ ይገኛል'' ብለዋል። በቀጣይ በምስራቅ አፍሪካ አካባቢ የማስፋፊያ ስራ ለመስራት ከኢትዮጵያ ለመጀመር ጥናት የማድረግ እቅድ እንዳላቸው ገልጸዋል። ከአፍሪ ሄልዝ ትሬዲንግ ጋር በጋራ ለመስራት የተደረገው ስምምነት በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ለማፍሰስ ምቹ ሁኔታዎች ላይ ጥናት ለማድረግ ሰፊ እድል የሚፈጥር መሆኑን ጠቁመዋል። አገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እያስመዘገበች ያለች አገር መሆኗ፣ አቅም ያላቸው የህክምና ባለሙያዎች መኖርና የሕዝቡ ቁጥር በኢትዮጵያ ለመስራት ሳቢ ከሆኑ ሁኔታዎች እንደሆኑ ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም