የጠቅላይ ሚኒስትሩ የኖቤል ሽልማት ከልዩነት ይልቅ ጠንካራ አንድነትን ለመፍጠር ያግዛል

113

ኢዜአ፤ ታህሳስ 3/2012 የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰላም ኖቤል ሽልማት በኢትዮጵያዊያን መካከል ልዩነትን ከማስፋት ይልቅ ጠንካራ አንድነት እንዲፈጠር የላቀ እገዛ አለው ሲሉ የአማራ ክልል መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ገለፁ።

በጠቅላይ ሚኒስትሩ የኖቤል ሽልማቱ በማግኘታቸው የባህር ዳር ከተማ ነዋሪዎች በውይይት ደስታቸውን ገልፀዋል።

በውይይቱ ላይ የተገኙት ዳይሬክተሩ አቶ ጌትነት ይርሳው እንዳሉት የኖቤል ሽልማቱ ለሰላም የተከፈለውን ዋጋ የዓለም ህዝብ እንዲያውቅ ያደረገ ነው።

ሽልማቱ በፖለቲካ፣ በብሔር፣ በሃይማኖት፣ በቋንቋና መሰል ጉዳዮች ልዩነቶች ቢኖሩም በዜጎች መካከል ተቻችሎ በመኖር ጠንካራ አንድነት እንዲፈጠር የሚያግዝ መሆኑን ገልፀዋል።

“የቀደሙ አባቶች አንድነታቸውን ጠብቀው ያቆዩዋትን አገር ወጣቱ ትውልድ እርስ በርስ ከመገፋፋትና ከመነቃፍ ወጥቶ ለአገሩ አንድነት በጋራ ሊሰራ ይገባል” ብለዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሽልማት ለመላው ኢትዮጰያውያን ኩራት ከመሆኑ ባለፈ በቀጣይ ለሚከናወኑ በርካታ የሰላም፣ የልማትና መሰል ሥራዎች ስንቅ እንደሚሆንም አቶ ጌትነት ተናግረዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀጣይ ሥራ የተሳካ እንዲሆንም የአማራ ህዝብና መንግስት ከጎናቸው ሆኖ እንደሚያግዝና እንደሚደግፍ አስታውቀዋል።

ዶክተር አብይን ለዓለም የሰላም ኖቤል ሽልማት እንዲበቁ ካደረጓቸው ዋነኛ ሥራዎቻቸው አንዱ ሴቶችን ወደ አመራርነት ያመጡበት በመሆኑ ነው ያሉት ደግሞ የመድረኩ ተሳታፊ ወይዘሮ ብርሃን ሁልጊዜ ናቸው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሴትን ማብቃትና በአመራር ከወንዶች እኩል ማድረግ አንዱ የስልጣኔና የእድገት መለኪያ ነው በሚል ለሴቶች የሰጡት እድል በርካቶች ከጓዳ እንዲወጡ መነቃቃት መፍጠሩንም አመልክተዋል።

የተቀበሉት የሰላም ኖቤል ሽልማትም የበለጠ ጠንክረው እንዲሰሩና በየአካባቢው የሚስተዋሉትን የመልካም አስተዳደር ችግሮችንና ሌሎች የህዝብ ጥያቄዎችን ለመፍታት እንደሚያግዛቸው ተናግረዋል።

“የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰላም ኖቤል ሽልማት ወጣቱን ለሰላምና ልማት እንዲነሳሳ ያደረገ ነው” ያለው ደግሞ ወጣት አሰፋ አገኘ ነው።

በቀጣይም የጠቅላይ ሚኒስትሩን በጎ ተግባር በመመልከት የበለጠ ውጤታማ እንዲሆኑ እንደወጣት ከጎናቸው ለመቆም መነሳቱን ገልጿል።

በውይይቱ የከተማ አስተዳደሩ አመራሮችና ነዋሪዎች ተገኝተዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም