በጋምቤላ ክልል በገቢ አሰባሰብ፣ በፕሮጀክት ግንባታና በልማት ዘርፎች የአፈጻጸም ክፍተት ታይቷል - የክልሉ ምክር ቤት አባላት

56
ጋምቤላ ሰኔ15/2010 በጋምቤላ ክልል ባለፉት ዘጠኝ ወራት በገቢ አሰባሰብ፣ በፕሮጀክት ግንባታና በሌሎችም የልማት ዘርፎች የአፈጻጸም ክፍተት መኖሩ ተገለጸ፡፡ በክልሉ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የተከናወኑ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎችን የዕቅድ አፈጻጸም የሚገመግም መድረክ በጋምቤላ ከተማ ተካሂዷል፡፡ የክልሉ ምክር ቤት አባላት በመድረኩ ላይ እንዳሉት በክልሉ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በጤናው ዘርፍ የእናቶችና የህጻናትን ሞት በመቀነሰና በትምህርት ተደራሽነት በኩል የተሻለ አፈጻጸም ቢኖርም በሌሎች የልማት ዘርፎች ውስንነቶች ተስተውለዋል። በተለይም በገቢ አሰባሰብ፣ በፕሮጀክቶች አፈጻጸም፣ በወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በትምህርትና በጤና አገልግሎት ጥራትና በሌሎችም ዘርፎች ክፍተቶች የጎሉ ናቸው። ከምክር ቤቱ አባላት መካከል አቶ ቲቶ ሃዋሪያት በሰጡት አስተያየት እንዳሉት በክልሉ ገቢ በአግባቡ ባለመሰብሰቡ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት እንቅስቃሴዎች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እየተፈጠረ ነው። አቶ ቲቶ እንዳሉት በክልሉ ያለውን እምቅ የገቢ አቅም በአግባቡ በመሰብሰብ የህዝብ የልማት ጥያቄና በየዓመቱ የሚታየውን የበጀት ጉድለት ለመፍታት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ ይገባል፡፡ በክልሉ ግንባታቸው በመካሄድ ላይ ያሉ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ባለመከናወናቸው ለታለመላቸው ዓላማ እየዋሉ አለመሆኑን የገለጹት ደግሞ ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ ሙሴ ጋጄት ናቸው፡፡ "በክልሉ የተጀመሩ ፕሮጀክቶች በአፋጣኝ ተጠናቀው ለአገልግሎት እንዲበቁ ለማድረግ የምክር ቤቱ አባላት ትኩረት ሰጥተን ልንሰራ ይገባል" ብለዋል፡፡ አቶ ኦኬሎ ኡማን የተባሉ የምክር ቤቱ አባል በበኩላቸው ባለፉት ዘጠኝ ወራት በክልሉ ወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማድረግ የተከናወኑ ሥራዎች ቢኖሩም ከዕቅዱ አንጻር በቂ እንዳልሆኑ ገልጸዋል፡፡ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሰናይ አኩዎር በበኩላቸው በክልሉ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የተለያዩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች ሲከናወኑ ቢቆዩም እቅዱን ከማሳካት አንጻር ክፍተቶች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡ በተለይም በአገልግሎት አሰጣጥ፣ በማህበራዊ ተቋማት የጥራት ችግርና በኢኮኖሚው ዘርፎች የተስተዋሉ ውጤትን መሰረት ያላደረጉ እንቅስቃሴዎች ባለፉት ዘጠኝ ወራት በቀዳሚነት የተስተዋሉ ችግሮች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም በቀጣይ ሕብረተሰቡ የሚያነሳቸውን የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታትና ተገልጋዩ ፈጣን አገልግሎት እንዲያገኝ በክልሉ መንግስት በኩል በትኩረት እንደሚሰራ አስረድተዋል፡፡ እንደ አቶ ሰናይ ገለጻ፣ በክልሉ የተጀመሩ የልማትና የመልካም አስተዳድር ሥራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል በየደረጃው የሚገኙ አመራሮችና የምክር ቤት አባላት ቁርጠኛ ሆነው መስራት ይኖርባቸዋል፡፡ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች የሚታዩ የጥራት ችግሮችን በመፍታት በኩልም በቀጣይ በምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎች አማካኝነት የተጠናከረ የቁጥጥርና የክትትል ሥራ እንደሚሰራ አስታውቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም