ኢትዮጵያውያንን ያኮራ ተግባርና በማህበራዊ ትስስር ድረ ገፆች የተገለፁ ስሜቶች

523

በሀብታሙ አክሊሉ (ኢዜአ)

የኖርዌይ ዋና ከተማ ኦስሎ ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያዊነትን ስታወድስ፣ ስታገዝፍ እና በአለም አደባባይም የታላቅነት ምስክርነትን ስትሰጣቸው ውላለች። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድም በኦስሎ ከተማ በሚገኝ እና በአብረቅራቂ ምንጣፍ በተንቆጠቆጠው አዳራሽ ውስጥ በተከናወነው ልዩ ፕሮግራም ላይ አብይ ጉዳይ ሆነው አምሽተዋል። በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰላም ኖቤል ዕውቅና ስነ ስርአት ላይም እንደ ቤቲ ጂ የመሰሉ አርቲስቶች ሌሎች የኢትዮጵያዊነት ድምቀቶች ነበሩ። በጠቅላይ ሚኒስትሩ መሳጭ እና ማራኪ ንግግር ላይ የአርቲስቶቹ ኪነ ጥበባዊ ዝግጅት ሲታከልበት ምን ጊዜም ከእዝነ ህሊና ሊጠፋ የማይችል ትዝታን በኦስሎ ታዳሚያን ዘንድ አጭሮ አልፏል ለማለት ያስችላል። ሃገራችንም ሌሎች በዘመናት አንዴም ሊያገኙት የማይችሉትን ክብር ተጎናፅፋለች።

የጠቅላይ ሚኒስትሩን የሰላም የኖቤል ሽልማት የዕውቅና ስነ ስርአትን ተከትሎም በርካቶች የማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም ስሜታቸውን ለተከታዮቻቸው እያጋሩ ይገኛሉ። በተለይ የፌስቡክና ሌሎች የማህበራዊ ትስስር ድረ ገፅ በመጠቀም ስሜቶቻቸውን እያጋሩ ከሚገኙ ተከታዮች አብዛኞቹ የኖርዌይ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት ቤሪት ሬይስ አንደርሰን ያስተላለፉት መልዕክት ላይ ትኩረታቸውን አድርገው ነበር።

“ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ ናት፤ ከዚህ አንፃር ሁላችንም ኢትዮጵያውያን ነን።” በማለት የተናገሩትን በርካቶች የማህበራዊ ትስስር ድረ ገፅ ተጠቃሚዎች አጉልተው (ስወዱት)ላይክ ሲያደርጉ፣ ሲያጋሩ እና የንግግሩ ቃላትን በተለያዩ ቀለማት በማሸብረቅ ለማጋራት ሞክረዋል። ይህንኑ መልዕክት ተንተርሰው ደግሞ የማህበራዊ ትስስር ድረ ገፅ ተጠቃሚዎቹ የተለያዩ ሃሳቦችን አንፀባርቀዋል። ሃሳቦቹም ምንም ሳይቆራረጡ እንደወረዱ እንዲህ ቀርበዋል።

የአዲስ ሃሳብ

‘የዘንድሮው የኖቤል ሽልማት ሥነስርዓት እንኳን እኛ እርስ በርስ ይቅርና ከዓለም ጋር የጋራ ታሪክ እንዳለን ያሳየ ሐቅ ነው።’

SBS Amharic· 

ኢትዮጵያ የመጀመሪያው የሰው ዘር መገኛ በመሆኗ ሁላችንም ኢትዮጵያውያን ነን“ – የኖቤል ሰላም ሽልማት ኮሚቴ ሰብሳቢ

 Amy Geogane  

#ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ ናት፣ ከዚህ አንፃር #ሁላችንም ኢትዮጵያውያን ነን።

ቤሪት ሬይስ አንደርሰን የኖርዌይ የኖቤል ኮሚቴ ሊቀመንበር በጠቅላይ ሚኒስቴር ዶክተር አብይ አህመድ የኖቤል ሽልማት ፕሮግራም ላይ ከተናገሩት የተወሰደ

ከላይ የተጠቀሱት ሃሳቦች ለአብነት ቀረቡ እንጂ የኖቤል ሽልማት ኮሚቴ ሰብሳቢዋ መልዕክት የማህበራዊ ትስስር ገፆችን አጨናንቆታል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኖቤል ዕውቅና ፕሮግራም ላይ ያደረጉት ንግግርም በርካቶችን በደስታ ድባብ ውስጥ ሆነው እንዲያነቡ አድርጓቸዋል። ሃገር በሰው ሃገር ሰማይ ስር ክብሯ ሲነገር፣ ዝናዋ በጠቅላይ ሚኒስትሯ ገድል ሲናኝ ከቶ እንዴት ደስ አያሰኝም! ብዙዎች በአዳራሽ ታዳሚም ሆነ በየቤቱ በየቴሌቪዝን መስኮቱ የተኮለኮሉ በሁኔታው ስሜታቸውን መቆጣጠር አቅቷቸው አንብተዋል፤ በደስታ ሲቃም ተሞልተዋል። ይህንን ሁኔታም በማህበራዊ ትስስር ድረ ገፆች ላይ አንፀባርቀዋል።

Poye Fekadu

በሬን ዘግቼ የዶ/ ዐቢይን የኖቤል ሽልማት ሥነ ሥርዐት በሰላም ስመለከት፣ የኖቤል ኮሚቴ ሊቀ መንበሯ ሴትዮ፣ “… in this sense, we all are Ethiopians” ስትል ምን እንዳስጮኸኝ አልገባኝም፡፡ “It was never colonialized by any western power.” ስትልማኢትዮጵያዊ ነኝእያልኩ በጎዳና እንዳልሮጥ የአውሮፓ ብርድ ነው ከበር ጨምድዶ የመለሰኝ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ንግግሩን ሲጨርስም፣ ከመቀመጫዬ ተፈናጥሬ ከታዳሚው እኩል እያጨበጨብሁ እግዚአብሔርን አመስግኛለሁ፡፡

ምን ፖለቲካን ብሸሸው፣ ይህንን መሸሽ አልቻልኩም!

ምናባቴ አደርጋለሁ?

Dinkneh Abachali እኔ ኢትዮጵያ ውስጥ ነኝ ፕሮግራሙን ምሽት በአሀዱ ቲቪ ስከታተል እራሴን መቆጣጠር አቅቶኝ ነበር። የደስታ እንባ!!! አሁን ደግሞ ስታፍ ቁጭ ብዬ የአንተን ፖስት ሳነብ ጩህ ጩህ አለኝ የሆነ ስሜት ፈንቅሎኝ ጀርባዬን ጨምድዶ ያዘኝ ዓይኞቼን የወረረው የእንባ ጭጋግ የሚተናነቅ ብርቱ ስሜት አነባሁ የደስታ ሲቃ ኢትዮጵያዊነት

Negash Abebe ተድላ እየተሰማቸው ነው።

ዛሬ /ሚር ዐቢይ አህመድ በታላቁ የዓለም መድረክ ላይ ኮርተው እጅግ አኩርተውናል። የንግግራቸው ምጥንነት፣ ማራኪ አቀራረብ እና ኃያል መልእክት እንባ ልተናነቅህ እያለኝ እጄን በአፌ ላይ ጭኜ እንድክታተል አድርጎኛል። የመርሀ ግብሩ መሪኢትዮጵያ የሰው ልጅ መገኛ ናትና ሁላችንም ኢትዮጵያውያን ነንሲሉ መስማት ደግሞ ሌላ ልብን በሀሴት የሚሞላ እና በቃላት ለመግለፅ የሚያስቸግር ልዩ ስሜት ፈጥሯል። እንኳን ደስ አለን! ኢትዮጵያ ለዘለአለም ትደስት!

Yehunie Belay

ክቡር / ዶክተር አብይ አህመድ ኢትዮጵያን በአለም መድረክ ከፍ ስላደረካት በጣም ደስ ብሎኛል፡፡ እንኳን ደስ ያለህ ! እንኳን ደስ ያለሽ ሀገሬ!

Tinsae Ethiopiawiwu 

የመላው ኢትዮጵያውያንን ታሪክ ማርሹን የቀየረበት ዕለት፤ ድሉ ለኦሮሞው፣ ለአማራው፣ ለትግሬው፣ ለጋምቤላው፣ ለደቡቡ፣ ለሶማሌው እና ዳር እስከዳር ላለው ህዝብ እኩልነት እና ሰላም ቁልፋችን ነው።

የማህበራዊ ትስስር ተጠቃሚዎቹ የስሜት አገላለፅ የተለያየ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ሁሉንም ለማቅረብ ያዳግታልና ከላይ ለአብነት የቀረቡትም ሁኔታውን በደንብ ይገልፁታል ብለን እንገምታለን። ከዚህም ሌላ የተለየ ሀሳብን በማንፀባረቅ ሁኔታውን የገለፁ ሰዎችም ነበሩ። ከነዚህም ውስጥ የሰርፀ ፍሬ ስብሃትን እና የዶ/ር በድሉ ዋቅጅራን ቀጥለን እንመልከት።

‘ታላቅ የሀገር ክብር በመሪዋ!!!’ የሚለውን መልዕክት ማህበራዊ ትስስር ድረ ገፁ የለጠፈው ሰርፀ ፍሬስብሃት አጠር ተደርጎ በቀረበው መልዕክቱ ብዙ ብሎበታል። የዶ/ር በድሉ ዋቅጅራን ደግሞ እንሆ፤

Bedilu Wakjira

/ አብይ አህመድ እንኳን ደስ አለህ!

ይህ የአንተ ጥረት ውጤት፣ የኢትዮጵያውያን መሻትና ተስፋ ነው፡፡ የዜጎች የልብ መሻት የሆነው ሰላም፣ በአንተ የልቦና ቀጥተኛነትና ብርሀን በሀገራችን ይሰፍን ዘንድ ምኞቴ ነው፡፡ ፍትህንና ሰላምን አጎናጽፈኸን የሚቀጥለውን አመት ኖቤል ከእኛ ከኢትዮጵያውያን ትቀበል ዘንድ አምናለሁ፡፡

የኖቤል ሽልማት ተቋም በትዊተር ገፅ አካውንቱ ላይ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በኖቤል ሽልማት ስነ ስርአት ላይ ከተናገሩት አጠር ያለና ገላጭ ፍሬ ሃሳብን ለጥፏል።

ሰላም ልክ በእንክብካቤ ተይዞ እንደሚያድግ ችግኝ ነው፤ ዛፎች ለማደግ ውሃና አፈር እንደሚፈልጉ ሁሉ ከሰላም የሚገኘውን ትሩፋት ለመቋደስ የማይናወጥ ቁርጠኝነት፣ ውስንነት የሌለው ትዕግስትና መልካም ፈቃደኝነትን ይጠይቃል።’ የሚል መልዕክትን ልጥፉ ይዟል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩም በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ላይ የተሰማቸውን ስሜት በዚህ መልኩ አጋርተዋል።

Abiy Ahmed Ali

ኦስሎ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ እስክትመስል ድረስ በኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማና በኢትዮጵያ ባነሮች ተውባ ሰነበተች፡፡ ሚዲያዎች ሁሉ ስለ ኢትዮጵያ በኩራት መሰከሩ፡፡ ኢትዮጵያን በድህነትና በጦርነት፣ በረሐብና በእልቂት የሚያውቋት ሁሉ አዲስ ታሪክ ሆነባቸው፡፡ በሩጫ ስናሸንፍ ነበር የሚያውቁን፤ ዛሬ ደግሞ በሰላም ሥራችን በዓለም አቀፍ መድረክ ስናሸንፍ አዩን፡፡ ከግሪን ላንድ እስከ ኒውዚላንድ፣ ከቺሊ እስከ ጃፓን ዓይኖች ሁሉ ወደ ኦስሎ ተተክለው ስለ ኢትዮጵያ ተመለከቱ፡፡

በመላው ዓለም ተበትነው የሚኖሩት ኢትዮጵያውያን የዜግነት ክብራቸውን ከፍ የሚያደርግ ሥራ በታሪክ ውስጥ ሲመዘገብ አዩ፡፡ ልጆቻቸው በባዕድ ሀገር በታሪካቸው ኮሩ፡፡ ሀገራቸው በምሳሌነትና በአርአያነት ስትነሣ በዓይናቸው ብሌን ተመለከቱ፤ ሰሙ፡፡ በዓረብ ሀገር የሚኖሩ ዜጎቻችን አሠሪዎቻቸው ወደታች ሳይሆን ወደላይ እንዲያዩዋቸው የሚያደርግ ታሪክ በዓለም አደባባይ ሲከወን ዕንባ በተሞሉ ዓይኖቻቸው አደነቁ፡፡

ሁለት ዓይነት ታሪክ ሲሠራ የዓለም ዓይኖች ታዘቡ፡፡ በጦርነት የምትታወቅ ሀገር የሰላም ሽልማት ተሸለመች፡፡ የሰላምን ዋጋ የሚያውቀው ዓለም፤ የሰላም ሽልማት በቀላሉ እንደማይገኝ የሚያውቁ የዓለም ዜጎች በደስታና በክብር አብረውን ከረሙ፡፡ ለሕዝቦች መቀራረብ፣ ለሕዝቦች መገናኘት፣ ለሕዝቦች ዕርቅና ሰላም መሥራት የሚያሸልም ተግባር መሆኑን የሚያውቁ ሁሉ፤ የቻሉ በኦስሎ ጎዳናዎች ተገኝተው፤ ያልቻሉ በየቴሌቭዥን መስኮቶች አፍጥጠው ክብር ሰጡን፡፡

በኦስሎ ያገኘነው ክብር የሀገራችን ጉዞ ከትናንት የዛሬው፣ ከዛሬውም የነገው እጅግ የተሻለ መሆኑን አመላክቶናል፡፡ ይህ ለኢትዮጵያውያን የመጀመሪያ እንጂ የመጨረሻ አይሆንም፡፡ በሰላም፣ በሳይንስ፣ በሥነ ጽሑፍ ገና ብዙ ኢትዮጵያውያን ወደ ኖቤል ሀገር ወደ ኖርዌይ ይመጣሉ፡፡

ዛሬ ያገኘነውን አክብረን አያሌ ኢትዮጵያውያን በዓለም አቀፍ መድረኮች ሀገራቸውን እንዲያስጠሩ እንሠራለን። ለዚህ ደግሞ ሁላችንም ሀገር የሚያስጠራ ጥረት እንድናደርግ ጥሪ አቀርባለሁ፡፡

የፈረንጆቹ 2019 መገባደጃ ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ብስራትን ሲያሰማን ሰንብቷል። በዕውቁ አለም አቀፍ ሚዲያ ሲ ኤን ኤን የአመቱ ጀግና ሴት ‘ሂሮ ኦፍ ዘ ይር’ የሚል ክብርን ካገኘችው ፍሬወይኒ መብርሃቱ የአመቱ የአየር መንገድ ዋና ስራ አስፈፃሚዎች ሽልማትን እስካገኙት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈፃሚ ተወልደ ገ/ማርያም ድረስ ኢትዮጵያውያን በአለም አደባባይ ነግሰው ሰንብተዋል። ከተጠቀሱት በተጨማሪ የሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የሳይካትሪስትና ኢፒዲሞሎጂ ዓለም አቀፍ ሽልማትን ያገኙት ፕሮፌሰር አታላይ አለም፣ የፕሪሚዮ ዓለም አቀፍ የስፖርታዊ ጨዋነት ሽልማት ክብርን ያገኘችው ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ፣ አፍሪማ በተሰኘው የአፍሪካ ባህላዊ ሙዚቃ ሽልማት ዘርፍ ያሸነፈው አርቲስት አብርሃም በላይነህ (ሻላዬ) በጥቂቱ ይጠቀሳሉ። ኢትዮጵያና ታታሪ ልጆቿ በአለም አቀፍ ደረጃ ለዕውቅና የበቁበት የሰሞኑ አይነት ድባብ ለከርሞም ያዝልቅልን!! አሜን