ወጣቶች የሰላም ኃይል እንዲሆኑ የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠየቀ

ኢዜአ ታህሳስ 02/2012…ወጣቶች የሰላም ኃይል በመሆን በሀገሪቷ ውስጥ የሚስተዋሉ ግጭቶች ለማስቆም የድርሻቸውን እንዲወጡ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠየቀ። "ወጣቶች ለሰላም "  በሚል መሪ ቃል ሀገር አቀፍ የሰላም ኮንፈረንስ ዛሬ አዳማ ከተማ ተጀምሯል። የጉባኤው ምክትል ፀሐፊ አቶ ሂሉፍ ወልደስላሱ በኮንፍረንሱ መድረክ  እንዳሉት በቅርቡ በሀገሪቱ እየተበራከቱ በመጡት ግጭቶች ውስጥ ወጣቶች ተሳታፊና ተጎጂዎችም ናቸው። በተሳሳተ መረጃና በስሜት በመገፋት ግጭቱ የሚያስከትለውን ጉዳትና ቀውስ ካለማመዘን ወጣቶች የሚሳተፉበት እንደሆነ አመላክተዋል። "ግጭቶች በባህሪያቸው ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል የሚጎዱ በመሆኑ ችግሮቹን ለማከምና ለማስወገድ ሁላችንም አንድ ሆነን መስራት አለብን "ብለዋል። በተለይም ወጣቶች የሰላም ኃይል መሆናቸውን ተገንዝበው በሀገሪቱ ውስጥ የሚስተዋሉ ግጭቶች ለማስቆምና አለመግባባቶች ለመፍታት በሚደረገው ጥረት የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል። በኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የክልል ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ መጋቢ ታረቁ ኃይለሚካኤል በበኩላቸው "አብሮነትን ከመንፈሳዊ አስተምሮ ጋር በመቃኘት በልዩነቶች ውስጥ ጠንካራ አንድነት መኖሩን ማሳየት አለብን "ብለዋል። በዚህም የኃይማኖት መሪዎችና ወጣቶች ልዩነትና አብሮነትን በጋራ ለማስኬድ መቻቻልና መከባበርን በማጎልበት ላይ በቅንጅት መስራት ይጠበቅባቸዋል። መጋቢ ታረቁ "በተለያዩ አካባቢዎች ባለመቻቻልና ባለመከባበር የሚፈጠረው ግጭት ሁሉንም የሚጎዱ በመሆኑ ወጣቶች በአርቆ አሳቢነት ልዩነትን በማክበር ለሀገር ሰላምና አንድነት መስራት ይጠበቅባቸዋል "ብለዋል። ለሁለት ቀናት በሚቆየው ኮንፍረንስ  ከተለያዩ የወጣት አደረጃጀቶች፣ ከሰላም ሚኒስቴርና ከኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ  የተወጣጡት አካላት እየተሳተፉ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም