የዶክተር አብይ ሽልማት ሁሉም ህብረተሰብ ለሰላም እንዲቆም ያነሳሳ ነው... አቶ ኦርዲን በድሪ

86

ኢዜአ ህዳር 2/2012 "የዶክተር አብይ የሰላም ኖቤል ሽልማት ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ለሰላም እንዲቆም ያነሳሳ ነው" ሲሉ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ተናገሩ።

ርዕሰ መስተዳድሩ ሽልማቱን አስመልክቶ በተዘጋጀው የደስታ መግለጫ ስነስርዓት ወቅት እንደገለጹት ዶክተር አብይ አህመድ የሰላም ኖቤል ተሸላሚ የሆኑት በሀገር ውስጥና በአፍሪካ ቀንድ  ላከናወኗቸው  አስደናቂ ተግባራት ነው።

"እያንዳንዱ ዜጋ ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ የማይተካ ሚና  ያለው  መሆኑን  ተገንዝበን ሁላችንም የድርሻችንን  ማበርከት ይጠበቅብናል" ብለዋል።

በጥላቻ ፣ መናናቅ እና የአንድ ወገን ፍላጎትን በማጉላት የሚገኝ ሰላም እንደማይኖር ጠቅሰው  የመቻቻልና የአብሮነት እሴትን በማጎልበት ለዘላቂ ሰላምና እድገት መተባበር እንደሚገባ አመልክተዋል።

ሽልማቱ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ለሰላም ዘብ እንዲቆም ያነሳሳ መሆኑን ገልጸው ይህንን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም በአንድነት መስራት እንደሚገባ   መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በክልሉ ምክር ቤት መሰብሰቢያ አዳራሽ በተዘጋጀው ስነስርዓት ከተሳተፉት መካከል ወይዘሮ ፈቲሃ በበኩላቸው የጠቅላይ ሚኒስትሩ  ሽልማት የአብሮነት እሴቶች እንዲጎለብት የሚያበረታታ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም ይቅር መባባልና አንድነትን በማጠናከር ለሀገሪቱ እድገት መስራት እንደሚገባ አመልክተዋል።

አቶ መሐመድ ዩስፍ  የተባሉት የሀገር ሽማግሌ በሰጡት አስተያየት  “ የዶክተር አብይ አህመድ ሽልማት የሁሉም ኢትዮዽያዊ  ነው፤ይህም ሁሉም ዜጋ ለሰላም ዋጋ መስጠት እንዳለበት ያስገነዘበ ነው" ብለዋል

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥረት በመደገፍ ሀገሪቱን ወደ ተሻለ ደረጃ ማሻገር ከሁሉም እንደሚጠበቅ የገለጹት ደግሞ አቶ በሐር አደም ናቸው።

የጠቅላይ ሚኒስትሩን የሰላም ኖቤል ሽልማት በማስመልከት በተዘጋጀው የደስታ መግለጫ ስነስርዓት  የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ፣የኃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች፣አባ ገዳዎች፣ወጣቶችና ሴቶች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም