ወጣቶች ለአገር ሰላም መረጋገጥ የድርሻቸውን መወጣት እንዲችሉ መደራጀት አለባቸው ተባለ

102
ኢዜአ ታህሳስ 2/2012 ''ወጣቶች ለአገር ሰላም መረጋገጥ የድርሻቸውን መወጣት እንዲችሉ መደራጀት አለባቸው'' ሲሉ የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን አባላት ገለጹ። አባላቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የ2019 የዓለም ሰላም ኖቤል ተሸላሚ በመሆናቸው ደስታቸውን ገልጸዋል። የፌዴሬሽኑ አባል ወጣት አስማማው ጥጋቡ በሰጠው አስተያየት ''ዘላቂ ሰላምን ለማምጣትም ወጣቱ ከቤቱ ጀምሮ የጎረቤቱንና የአካባቢውን ሰላም ሲጠብቅ የድምር ውጤቱ የአገር ሰላም ይሆናል'' ብሏል። በመሆኑም ሁሉም ዜጋ በሚችለው አቅም የድርሻውን ሲወጣና የመንግስት አመራሮችም በየደረጃው በመቀናጀት ሰላም ለማስጠበቅ በቁርጠኝነት ከወጣቱ ጋር በጋራ ሊሰሩ እንደሚገባም አስገንዝቧል። ወጣቱም በሌሎች አጀንዳዎች እንዳይጠለፍ ያለውን ጥያቄ አደራጅቶ በማቅረብ ራሱን ከጽንፈኛ ሀይሎች መከላከል እንዳለበት ገልጿል። ለአገር ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ ግንባታ ወጣቶች የድርሻቸውን መወጣት የሚችሉ ሲደራጁ እንደሆነ አመልክቷል። ሌለው አስተያየት ሰጪ ፌዴሬሽኑ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወጣት ሙህዲን ናስር የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰላም የኖቤል ሽልማት በወጣቱ ዘንድ መነቃቃት እንደሚፈጥርና የአገርን ታሪክ ለመቀየር አስተዋኦ እንደሚኖረው ተናግሯል። ''በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሰላም ባላቸው ቁርጠኝነት በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ሰላም ማስፈናቸው ትልቅ ክብር ይገባዋል'' ብሏል። በአገሪቱ እየታየ ያለውን አለመረጋጋትና የእርስ በርስ ግኘኑነት ማስተካከል ላይ ትኩረት በመስጠት ወጣቱ ሊሰራ እንደሚገባ አስገንዝቧል። ወጣት ኤርሚያስ ማቲዎስ በበኩሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሰላም ኖቤል አሸናፊነት ክብር ያበቃቸው ለሰላም ያላቸው ቁርጠኝነት በመሆኑ ወጣቶች ይህንን አረዓያነት መከተል እንዳለባቸው ጠቁሟል። ''የአገሪቱን ሰላም እውን ለማድረግም ሁሉም ወጣት በጋራና በትጋት መስራት ይገባዋል'' ብሏል። እንዲሁም ሰላም የሚጀመርው ወንድምን፣ እህትን፣ ቤተሰብንና አካባቢን በመጠበቅ እንደሆነና የጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሰላም ያበረከቱትን አስተዋዕኦ ፈር በመከተል ሁሉም ለሰላም ዘብ መቆም እንደሚገባው በመግለጽ ወጣት ኤርሚያስ መልዕክቱን አስተላልፏል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም