የተሸከርካሪ አደጋ ተጎጂዎች ተገቢውን የህክምና አገልግሎት አያገኙም---የመድን ፈንድ አስተዳደር ኤጀንሲ

97
ኢዜአ ታህሣሥ 2 /2012 የተሸከርካሪ አደጋ ተጎጅዎች ነፃ የሆነው አስቸኳይ የህክምና አገልግሎት በተገቢው እያገኙ አለመሆኑን የመድን ፈንድ አስተዳደር ኤጀንሲ አስታወቀ። በኤጀንሲውና በጤና ሚኒስቴር አስተባባሪነት የተሽከርካሪ አደጋ ተጎጂዎች የአስቸኳይ ህክምና አገልግሎትን ለመገምገም የተዘጋጀ የምክክር መድረክ በአዳማ ከተማ ተካሂዷል። የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሽመልስ ታምራት እንደገለጹት የተሸከርካሪ አደጋ ተጎጂዎች አስቸኳይ የህክምና አገልግሎት ከግልም ሆነ ከመንግሥት ጤና ተቋማት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በነፃ እንዲያገኙ መንግሥት በአዋጅ ደንግጓል። ይህንን አክብረው በሃገሪቱ ካሉት ከ4 ሺህ በላይ የህክምና ተቋማት ውስጥ አስቸኳይ ህክምና አገልግሎቱን እየሰጡ ያሉት ሁለት ነጥብ ስድስት በመቶ እንደማይበልጡ አመልክተዋል። ኤጀንሲው የአስችኳይ ህክምና አገልግሎት አሰጣጥ መመሪያ በማውጣት ለህክምና ተቋማት ያሰራጨ ቢሆንም በዚህ መሰረት አገልግሎቱን እየሰጡ ያሉት አነስተኛ ናቸው። በዚህም ምክንያት አገልግሎቱ ለዜጎች ተደራሽ አለመሆኑን አስረድተዋል። የተዘረጋው የአሠራር ስርዓት በጤና ሚኒስቴርና በተዋረድ የዘርፉ መስሪያ ቤቶች ግልጽነትና ተጠያቂነት በሚያስከትል መልኩ እየተሰራ አይደለም። ኤጀንሲው ቁጥጥር ካደረገባቸው ክልሎች ውስጥ ኦሮሚያ፣ትግራይና አማራ ክልልች የሚገኙ አብዛኛዎቹ የግል ሆስፒታሎች የአስቸኳይ ህክምን አገልግሎት እንዳልጀመሩ ማረጋገጣቸውን አቶ ሽመልስ ጠቅሰዋል። በተለይ የግል ህክምና ተቋማት ከ2 ሺህ ብር በላይ የሚበልጥ ጉዳት የደረሰበትን ተጎጂ ምንም ዓይነት እርዳታ ሳይሰጡ ወደ መንግሥት ሆስፒታል የመላክ ዝንባሌ መኖሩንም አስታውቀዋል። "ካለፈው ዓመት አጋማሽ ወዲህ ሰፊ የእንቅስቃሴ ስራ እየሰራን ነው" ያሉት አቶ ሽመልስ በተለይ በዘንድሮው የመጀመሪያ ሩብ ዓመት በአማራ፣ትግራይ፣ደቡብ፣ሐረሪ፣ ኦሮሚያ ክልልችና አዲስ አበባ አስተዳደር ብቻ 5 ሺህ 218 የተሸከርካሪ አደጋ ተጎጂዎች ህክምናወን እንዳገኙ ጠቁመዋል። ለነዚህ ተጎጂዎች ለህክምና የተከፈለው ተዘዋዋሪ ፈንድ 2 ሚሊዮን 841 ሺህ ብር መሆኑን አቶ ፍቃዱ አብራርተዋል። በጤና ሚኒስቴር የጽኑ ህክምና አገልግሎት ቡድን መሪ አቶ ፍቃዱ ያደታ በበኩላቸው ስራው አዲስ በመሆኑ በሚፈለገው ፍጥነት እየተጓዘ እንዳልሆነ ገልጸው “በቀጣይ አገልግሎቱን በመላ ሃገሪቱ ለማስፋፋት ጥረት ይደረጋል” ብለዋል። የመድን ፈንድ አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ወርቅነሽ ብሩ  መድረኩ የተዘጋጀው  በሀገሪቱ እየተሰጠ ያለውን አስቸኳይ ህክምና አገልግሎት ተደራሽነት፣ ጥራትና የተሰጠውን ትኩረት በመገምገም ግልጽነት፣ ተጠያቂነትና ቅንጅታዊ አሰራር  ለማስፈን የሚያስችል መግባባት ላይ ለመድረስ መሆኑን ተናግረዋል። ስራው ለተወሰኑ ተቋማት  ብቻ ሳይሆን የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ስለሚጠይቅ ድርሻቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ለማስቻል ጭምር መድረኩ መዘጋጀቱን አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም