ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በሰብል ላይ ጉዳት እያስከተለብን ነው — የባሌ ዞን አርሶ አደሮች

79

ኢዜአ ታህሳስ 2/2012 ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በደረሰ ሰብል ላይ ጉዳት እያስከተለብን ነው ሲሉ በባሌ ዞን የሚገኙ የአጋርፋና ሲናና ወረዳ አርሶ አደሮች ገለጹ።

የዞኑ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት በበኩሉ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በሰብል ምርት ላይ  ጉዳት እንዳያደርስ በዘመቻ ለመሰብሰብ የሚያስችል ግብረ ኃይል መቋቋሙን ገልፀዋል፡፡

የመኸር ምርት አዝመራና አሰባሰብ ላይ ለኢዜአ አስተያታቸውን ከሰጡ የአጋርፋ ወረዳ አሊ ቀበሌ አርሶ አደሮች መካከል አብዱ ሀሰን እንደተናገሩት አካባቢያቸው በአሁኑ ወቅት እየጠላ የለው ወቅቱን የልጠበቃ ዝናብ በበደረሱ ሰብሎች ላይ ጉዳት እያስከተለ ነው፡፡

አርሶ አደሩ እንዳሉት የዝናብ ሁኔታው ፋታ የሚሰጥ ባለመሆኑ የደረሱ ሰብሎችን  ለመሰብሰብ አስቸጋሪ አድርጎታል ብለዋል፡፡

በዞኑ እየጣለ ባለው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ የተወሰነውን የገብስ ምርት ያረገፈው ሲሆን ዝናቡ በዚሁ ከቀጠለ የከፋ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል የገለጹት ደግሞ ሌላው የዚሁ ወረዳ አርሶ አደር አህመድ ጠይብ ኡመር ናቸው።

ዝናቡ ቢያባራ የአጭዶ መውቂያ ማሽን በፍጥነት እንዲቀርብላቸው የሚመለከታቸው  የመንግስት አካላት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው ጠይቋል፡፡

የሲናና ወረዳ ነዋሪ ሴት አርሶ አደር ሀምዝያ በከር በበኩላቸው  በአካባቢያቸው እየጠላ ያለው ወቅቱን ያልጠበቃ ዝናብ በገብስ፤ ስንዴና ሌሎች የደረሱ ሰብሎች ላይ ጉዳት እያደረሰ ነው፡፡

ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በሰብል ላይ ጉዳት እንዳያደርስ የደረሱ ሰብሎችን በኮምባይነር እንዲታጨዱ ጥረት የጀመሩ ቢሆንም ዝናቡ ዳግም መዝነብ በመጀመሩ የምርት ስብሰባውን እያስተጓጐለው መሆኑን የተናገሩት ደግሞ ሌላው የሲናና ወረዳ አርሶ አደር ከማል አህመድ ናቸው፡፡

የዞኑ የእርሻና ተፈጥሮ ኃብት ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ኦሊቃ በበኩላቸው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በደረሰ ሰብል ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ህብረተሰቡን ያሳተፈ የምርት አሰባሰብ ዘዴን ለመከታል እየተሰረ ነው።

በዚህም ዝናቡ ጋብ ሲል ተማሪዎች፤ የፀጥታና የአገር መከላከያ ሰራዊትና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችን በማሳታፍ በዘመቻ ለመሰብሰብ የሚያስችል ከዞን እስከ ወረዳ ደረጃ ግብረ ኃይል መቋቋሙን ገልጾዋል፡፡

በባሌ ዞን በ2011/12 የመኸር ወቅት 335 ሺህ ሄክታር በዘር የተሸፈነ ሲሆን 10 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት መታቀዱን ከዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ኃብት ልማት ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

እስካሁን ባለው ሁኔታም በዘር ከተሸፈነው ማሳ መሰብሰብ የተቻለው 23 ሺህ 327 ሄክታር መሬት ላይ ያለውን ሰብል ብቻ ነው፡፡

በአንዳንድ የኢትዮጵያ ክፍሎች የተስተዋለው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ቀጣይነት ሊኖረው ስለሚችል ልዩ ትኩረት በመስጠት አስፈላጊውን ርብርብ በማድረግ የደረሱ ሰብሎችን እንዲሰበስቡ ብሔራዊ የሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም