በዞኑ የደረሰ ሰብል ሙሉ በሙሉ ተሰበሰበ

71
ታህሳስ 2/2012 ቀደም ሲል ያዳበሩትን አብሮ የመስራት ልምድ በመጠቀም የደረሰ ሰብላቸውን ሙሉ በሙሉ መሰብሰባቸውን በትግራይ የሰሜዊ ምእራብ ዞን ኢዜአ ያነጋገራቸው አንዳ አንድ አርሶ አደሮች ገለጹ፡፡ በዞኑ በመኽሩ ወቅት በተለያዩ ሰብሎች የተሸፈነው 237 ሺህ 265 ሄክታር ማሳ ሙሉ በሙሉ መሰብሰቡን የዞኑ አስተዳደር አስታውቋል፡፡ በዞኑ የላእላይ አድያቦ ወረዳ የማይአንበሳ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ነዋሪ አርሶ አደር በላይ ሀጎስ  “ለዘመናት ባዳበርነው አብሮ የመስራት ልምድ ተጠቅመን የደረሰውን ሰብላችን ፈጥነን በመሰብሰብ ከማንኛውም ጉዳት ተከላክለናል”ብለዋል፡፡ አርሶ አደሩ ባዳበረው የመተጋገዝ ባህልና ልምድ በሦስት ሄክታር ማሳ ላይ የነበረው ሰብላቸው በአጭር ጊዜ ሙሉ በሙሉ መሰብሰቡን ገልጸዋል፡፡ “ባለፉት ሦስት ዓመታት የመተጋገዝ ልምዳችን ተቀዛቅዞ ቢቆይም ዘንድሮ በአካባቢያችን የተከሰተው የበረሃ አንበጣ መንጋና ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ እንደ ማንቅያ ደውል ሆኖልናል'' ያሉት ደግሞ የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሕሉፍ አለሙ ናቸው፡፡ የደረሱ ሰብሎች ቅድሚያ በመስጠት  አርሶ አደሮች በህብረት በመስራት በአራት ሄክታር ማሳ ላይ የነበረውን ሰብላቸው ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብም ይሁን በአንበጣ  ጉዳት ሳይደርስበት መሰብሰባቸውን ተናግረዋል፡፡ በሁለት ሄክታር ማሳቸው የነበረው ሰብል መሰብሰቡን የተናገሩት ደግሞ በዞኑ የአስገደ ፅምብላ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ጎይቶኦም ይስማም አንዱ ናቸው። በደረሰው ሰብል የተጀመረው በህብረት የመስራት በጎ ተግባር በእንስሳት መኖ ላይ በመድገም  ላይ እንደሆኑ የተናገሩት ደግሞ አርሶ አደር ጎይተኦም ይስማም ናቸው፡፡ በዞኑ አስተዳደር የስነ አዝርእት ባለሙያ አቶ አዱኛ ገብራይ እንደገለጹት በመኽር ወቅቱ በተለያዩ ሰብሎች ከተሸፈነው ከ237 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በአንበጠና ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ ጉዳት ሳያደርስበት ሙሉ ለሙሉ መሰብሰቡን ገልጸዋል፡፡ ሰብል በደቦ  በመሰብሰብ ዘመቻ ላይ በዞኑ የሚገኙ ኤርትራዊያን ስድተኞችም በንቃት መሳተፋቸውን ገልጸዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም