በጅቡቲ ወደብ የአገልግሎት መጓተትን ማስቀረት የሚያስችል ዘመናዊ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሲስተም ሊዘረጋ ነው

69
አዲስ አበባ ሰኔ 15/2010 በጅቡቲ ወደብ የሚታየውን የአገልግሎት መጓተት ማስቀረት የሚያስችል የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሲስተም ሊዘረጋ መሆኑን የኢትዮጵያ ማሪታይም ጉዳይ ባለስልጣን አስታወቀ። የኢትዮጵያና የጅቡቲ የወደብ አገልግሎት ባለስልጣናት አዲስ የሚዘረጋውን "የጅቡቲ የወደብ ኮሚኒቲ ሰርቪስ" ሲስተምን አስመልክተው ከባለድርሻና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት አካሂደዋል። የኢትዮጵያ ማሪታይም ጉዳይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መኮንን አበራ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት በመጪው አንድ ወር ጊዜ ውስጥ በጅቡቲ የሚዘረጋው ሲስተም በወደቡ የሚታየውን የአገልግሎት መጓተትና የቅንጅት ጉድለት ማስቀረት ያስችላል። ይህም ወደ ውጭ እቃዎችን ለመላክና ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት ይወስድ የነበረውን ጊዜና ወጪ በከፍተኛ ደረጃ ለመቀነስና ለማሻሻል ያግዛል ብለዋል። አሁን የሚዘረጋው አዲሱ ሲስተም በዱባይ፣ በሲንጋፖር፣ በኬንያ ሞምባሳ ወደቦች እየተተገበረ የሚገኝ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህን ሲስተም በአግባቡ መተግበር ከተቻለ ውጤታማ መሆን እንደሚቻልም ተናግረዋል። በቀጣይም የሁለቱን አገራት የጉምሩክ አገልግሎት ለማቀናጀት፣ ለተጠቃሚ ምቹ ለማድረግ፣ የተሳለጠ የስራ ፍሰት እንዲኖር ለማድረግ እና ሁሉም የወደቡ ተጠቃሚዎች በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው በትኩረት ይሰራል ሲሉ ገልጸዋል። የጅቡቲ ማሪታይም ጉዳዮች ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ ሚስተር ዋርስማ መሐመድ በበኩላቸው አዲስ የሚዘረጋው ሲስተም በአሁኑ ወቅት በጅቡቲ ወደብ አገልግሎት ለማግኘት የሚፈጀውን ጊዜና ወጪ በግማሽ ለመቀነስ ያለመ ነው ብለዋል። ሲሰተሙ በሶስት ምዕራፍ ተከፋፈሎ የሚተገበር መሆኑን ጠቁመው፤ ይህም በመጪዎቹ ሁለትና ሶስት ወራት ጊዜ ውስጥ ስምንት ሰዓት ይፈጅ የነበረውን አገልግሎት ወደ 50 በመቶ በመቀነስ አራት ሰዓት እንዲፈጅ ለማድረግ ያስችላል። በቀጣዩ ስምንት ወራት ደግሞ አገልግሎቱን ሙሉ ለሙሉ ወደ አንድ ስዓት ለማድረስ የሚሰራ መሆኑን ተናግረዋል። ይህም ጊዜና ወጪን ትርጉም ባለው መልኩ በመቀነስ ምርታማነትን ለመጨመር፣ ብቃት፣ ቅልጥፍናና ጥራትን ለማረጋገጥ እንዲሁም በዘፈቀደ የሚሰሩትን የዋጋ ትመና ትግበራ ያስቀራል ሲሉ አክለዋል። የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ሲሰተሙ የሚዘረጋው ሁሉንም የወደብ አገልግሎቶች በአንድነት አቀናጅቶ የወደብ ተገልጋዮች ጊዜና ወጪ የሚቀንስ መሆኑን ገልጸዋል። አቶ ፋሲል ታደሰ የተባሉ አስተያየት ሰጪ አዲስ በሚዘረጋው ሲስተም የወደብ አገልግሎቱን ዘመናዊ ማድረጉ ወቅቱን የጠበቀ መሆኑን ጠቅሰው፤ ሲስተሙ እቃ ለማስገባትና ለማስወጣት ብቻ ሳይሆን የቁም ከብትና የመሳሰሉት አገልግሎቶችንም አቀናጅቶ ቢሰራ ጥሩ ነው ብለዋል። ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ ብሩክ ግዛቸው በበኩሉ የሚዘረጋው ሲስተም ከግንዛቤ እጥረት አላስፈላጊ መጉላላት እንዳያስከተል ለሁሉም ባለድርሻ አካላት፣ በተለይም ከኢትዮ-ጅቡቲ ለሚመላለሱ ሹፌሮች የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ እንዘጋጅ ጠይቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም