የጥምቀት በዓል በዩኔስኮ የማይዳሰስ ቅርስ ሆኖ ተመዘገበ

255

ኢዜአ፤ ታህሳስ  3/2012 የጥምቀት በዓል በተባበሩት መንግስታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ደርጅት /ዩኔስኮ/ የማይዳሰስ ቅርስ ሆኖ ተመዘገበ።

ዩኔስኮ የጥምቀት በዓልን በማይዳሰሱ ቅርሶች መዝገብ ውስጥ ማስፈሩን አስታውቋል።

የጥምቀት በዓል የእየሱስ ክርስቶስን በዮርዳኖስ ወንዝ መጠመቅ መታሰቢያ በማድረግ በመላ ኢትዮጵያ በታላቅ ድምቀት የሚከበር በዓል መሆኑን ድርጅቱ አስታውቋል።

በዓሉ በዋዜማው ታቦታትን ወደ ማደሪያቸው በመሸኘት መከበር የሚጀምር ሲሆን ሌሊቱን በተለያዩ ሃይማኖታዊ ስርዓቶችና በቅዳሴ ያሳልፋሉ።

ንጋት ላይ የጥምቀትና ሌሎች ሃይማኖታዊ ክንውኖች ከተካሄዱ በኋላ ታቦታቱ በምዕመናን መንፈሳዊና ባህላዊ ጭፈራዎች ታጅበው ወደየደብራቸው ይመለሳሉ።

የበዓሉን መጠናቀቅ ተከትሎ ታቦታት ከማደሪያቸው ወደ ቅድስት ቤተክርስቲያናቸው የሚመለሱት በታላቅ አጀብ እልልታና ሆታ መሆኑ በዩኒስኮ ተጠቅሷል።

የጥምቀት በዓል በአገሪቷ በደማቅ ሁኔታ ከሚከበሩ በዓላት ቀዳሚው ሲሆን በተለይ በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ታላቅ ቦታ የሚሰጠው ነው።