ሚኒስቴሩ ለወጭ ንግድ ማነቆ የሆኑ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል ስርዓት መዘርጋት አልቻለም – የፌደራል ዋና ኦዲት

362

ኢዜአ ታህሳስ 1/2012 የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ለወጭ ንግድ ማነቆ የሆኑ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል ስርዓት መዘርጋት አለመቻሉን የፌደራል ዋና ኦዲተር ግኝት እንደሚያመላክት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገለጸ።

በምክር ቤቱ የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የፌደራል ዋና ኦዲተር የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከ2008 እስከ 2010 ዓ.ም የወጪ ንግድ አፈጻጸም ላይ ባከናወነው የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት ላይ ከተቋሙ አመራሮች ጋር ተወያይቷል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ መሃመድ የሱፍ እንደተናገሩት ሚኒስቴሩ ለወጭ ንግድ ማነቆ የሆኑ ችግሮችን በጥናት በመለየት ከመሰረቱ ለመፍታት አለመቻሉ በፌደራል የዋና ኦዲት ሪፖርቱ ተመልክቷል።

በመሆኑም የቀረቡ የኦዲት ጉድለቶችን ለማረም የሚያስችል የድርጊት መርሃ ግብር በአፋጣኝ በማዘጋጀት ወደ ስራ መግባት ይኖርበታል ብለዋል።

የቋሚ ኮሚቴው አባላት እንደገለጹት ሚኒስቴሩ ምርቶችን በአይነትና በብዛት ለአለም ገበያ ማቅረብ የሚቻልበትን ስርዓት ባለመዘርጋቱ የወጭ ንግድ አፈጻጸሙ ዝቅተኛ ነው።

በወጪ ንግድ ላይ ለሚሳተፉ አካላት በቂ ድጋፍ፣ ክትትልና የጥራት ቁጥጥር አለማድረግ፣ በላኪና በገዥ ድርጅቶች መካከል የሚፈጸሙ ስምምነቶች ላይ የሚፈጸሙ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል መመሪያ አለመኖርና ሌሎች የኦዲት ግኝቶችን አንስተዋል።

የወጭ ንግድ ፍቃድና ለማበረታቻ የሚሰጠው ብድር ለታለመለት ዓላማ መዋሉና ላኪዎች ባዘጋጁት የወጪ ንግድ እቅድ መሰረት ኮንትራት እንዲገቡና እንዲልኩ ክትትልና ድጋፍ ከማድረግ አንጻር ክፍተቶች መኖራቸውንም ጠቅሰዋል።

በወጪ ንግድ የተሰማሩ አንዳንድ ላኪዎች በአነስተኛ ዋጋ በመላክ የኤክስፖርቱን ኪሳራ በገቢ ምርት በማካካስ የአገር ውስጥ የገበያ ዋጋ እንዳይረጋጋ ተጽዕኖ በማድረግና አገሪቷ ከውጭ ምንዛሪ የምታገኘውን ገቢ እንዲቀንስ የማድረግ ችግሮችንም ከኦዲት ግኝቶች መካከል አክለዋል።

በመሆኑም ላኪዎች የሚልኳቸው ምርቶች በዓለም ገበያ እንድሸጡና አገሪቷ ተገቢውን ገቢ እንድታገኝ የሚያስችል አሰራር መዘርጋት እንደሚገባም ተናግረዋል።

የንግድና አንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋናው አረጋ በሰጡት ምላሽ የወጪ ንግድ ላይ ያሉትን ክፍተቶች ለመፍታት በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት የሚመራ ብሄራዊ የኤክስፖርት ኮሚቴ መቋቋሙን ገልጸዋል።

በተለያዩ ተቋማት በተበታተነ መልኩ የሚመራውን ዘርፉንም በብሄራዊ ኮሚቴው አስተባባሪነት ክትትል እንደሚደረግ ገልጸው በአጭርና በረጅም ጊዜ የሚፈቱና በዘርፉ ያሉ ችግሮችም ተለይተው እየተሰራባቸው ነው ብለዋል።

የወጪ ንግድ አፈጻጸም ዝቅተኛ ለመሆኑ አንደኛው ችግር የምርቶች በአይነትና በጥራት በመጠን አነስተኛ መሆን ሲሆን ይህን ችግር ለመፍታት ከባለ ድርሻ አካላት ጋር የሚሰሩት ስራዎችም ተጠናክረው ይቀጥላሉ ነው ያሉት።

ሚኒስትር ዴኤታው እንደገለጹት በላኪና ገዥዎች መካከል የሚደረጉ ስምምነቶች ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታትም መመሪያ እየተዘጋጀ ነው ብለዋል።

የወጪ ፍቃድ አሰጣጥና የማበረታቻ ስርዓት ላይ ያለውን ክፍተት ለመፍታትም ጥናት እየተካሄደ ነው ብለዋል።

በቅርቡ ረቂቅ የጥናት ውጤቱ ይፋ እንደሚደረግና በጥናቱ መሰረት ወደ ተግባር እንደሚገባም አምባሳደር ምስጋናው ገልጸዋል።

የንግድ መረጃ አደረጃጀት ለመፍጠር የተጀመሩ ስራዎች መኖራቸውንም አክለዋል።

የፌደራል ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ዱቢሶ በበኩላቸው ሚኒስቴሩ የኦዲት ግኝቶችን ማስተካከል የሚያስችል የድርጊት መርሃ ግብር ማዘጋጀትና ተገቢውን እርምጃዎችን በመውሰድ ለባለ ድርሻ አካላት ማሳወቅ እንደሚኖርበት ተናግረዋል።

የወጪ ንግዱ ላይ ያሉ ማነቆዎችን ለመፍታት የሚያስችልና የተሻለ ተሞክሮ ያላቸውን አገራት ልምድ ያገናዘበ ስትራቴጂ ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።

የተቋቋመው ብሄራዊ የኤክስፖርት ኮሚቴ በዘርፉ ያሉትን የቅንጅትና ሌሎች ክፍተቶችን መፍታት እንደሚኖርበትም ዋና ኦዲተሩ አሰስበዋል።