በሀሰተኛ ሰነድ ሲጓጓዝ የተገኘ መድኃኒትና ልባሽ ጨርቅ በቁጥጥር ስራ ዋለ

237

ታህሳስ 1/2012 ከሰባት ሚሊዮን 700 ሺህ ብር በላይ ግምት ያለዉ መድኃኒትና ልባሽ ጨርቅ በሀሰተኛ ሰነድ በተሽከርካሪ ሲጓጓዝ በቁጥጥር ስር መዋሉን የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ገለጸ።
በኮሚሽኑ የኮምቦልቻ ቅርንጫፍ የህግ ተገዥነት ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ከፍያለው ቢያዝን ለኢዜአ እንድገለጹት ንብረቱ የተገኘው ትናንት ሌሊት ከደሴ መስመር ወደ አዲስ አበባ ሲጓጓዝ በነበረ ኮድ 3-45074 ኢት የሆነ ጭነት ተሽከርካሪ ላይ ነው።

በዚህም በሀሰተኛ ሰነድ የተለያየ የህክምና መድኃኒትና ልባሽ ጨርቅ ጭኖ ሲጓዝ በቁጥጥር ስር መዋል ተችሏል።

መቆጣጠር የተቻለውም የኮሚሽኑ ሰራተኞች ከአማራ ክልል የጸጥታ ኃይሎች ጋር በመተባበር በቃሉ ወረዳ ሀርቡ ከተማ ላይ ባደረጉት ድንገተኛ ፍተሻ  እንደሆነ ተመልክቷል።

የመኪናው አሽከርካሪ ንብረቱን ጥሎ ለጊዜው ከአካባቢው ቢሰወርም የጸጥታ ኃይሉ ለመያዝ ክትትል እያደረገበት መሆኑን አቶ ከፍያለው ተናግረዋል።

አሽከርካሪዎች  ሀገርና ህዝብን ከሚጎዳ ወንጀል ከመሳተፍ እንዲቆጠቡም መልዕክታቸው አስተላልፈዋል።

በሐሰተኛ ሰነድ እቃዎችን  ለማሳለፍ የሚደረገው ጥረት ዘንድሮ  ብቻ ይህ ለሦስተኛ ጊዜ እንደሆነም ተመልክቷል።