የነገው የድጋፍ ሰልፍ በኢትዮጵያዊነት መንፈስና አንድነት እንዲደረግ አስተባባሪ ኮሚቴው ጥሪ አቀረበ

72
አዲስ አበባ ሰኔ 15/2010 በነገው ዕለት ለሚካሄደው የድጋፍ ሰላማዊ ሰልፍ ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያዊነት መንፈስና አንድነት ሊያደርጉት እንደሚገባ አዘጋጅ ኮሚቴው ጥሪ አቀረበ። ሠልፉ በሰላምና በስኬት እንዲጠናቀቅ ህብረተሰቡ ኃላፊነቱን እንዲወጣም ጠይቋል። የኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ጉደታ ገለልቻ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳሉት፣ ሰልፉ  እንደ አገር ለመጀመሪያ ጊዜ መንግስት የጀመራቸውን የሰላም፣ የፍትህና ዴሞክራሲ ለውጦችን ለመደገፍ በህዝብ የተዘጋጀ ነው። "ያለውን ለውጥ እናበርታ! ዲሞክራሲውን እንደግፍ" በሚል መሪ ሃሳብ የሚካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ የማንም ሳይሆን ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሃይማኖት፣ በማንነት፣ በፖለቲካና አስተሳሰብ ልዩነት ሳይገደብ የሚወጣበት ቀን መሆኑንም አቶ ጉደታ ገልጸዋል። ''አገራችን በቅርብ ጊዜ ከነበረችበት ስጋት ተላቃ  የተገኙ የነጻነት፣ ፍትህና ዴሞክራሲ  ድሎችን ለማስቀጠል ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚሳተፍበት የምስጋና ቀን ነው'' ብለዋል። በመሆኑም የሰልፍ ስነ ስርዓቱ በሰላምና ያለምንም ችግር እንዲጠናቀቅ፣ ሰልፉን የሚያደናቅፉ ነገሮች እንዳይከሰቱ ኅብረተሰቡ የበኩሉን ሚና ሊወጣ እንደሚገባም ኮሚቴው አሳስቧል። በተለይም የድጋፍ ሰልፉን ሊያስተጓጉሉ የሚችሉ አዋኪ ነገሮች ሲስተዋሉ ህብረተሰቡ ለጸጥታ አካላት በመጠቆም አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግም ጠይቋል። ሰልፉ ከአዲስ አበባና በዙሪያዋ ከሚገኙ ከተሞች የሚመጡ ህዝቦች ስለሚኖሩበት የፌደራል፣ የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽኖች ለጸጥታ ትብብር ለማድረግ ቃል መግባታቸውን አቶ ጉደታ ጠቁመዋል። ሰልፉን የሚያስተባብሩ ከ2ሺህ እስከ 3ሺህ የሚሆኑ የሰልፍ አስተባባሪዎችም በየአካባቢው መሰማራታቸውን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም