ተቋሙ 43 የመርከብ መሃንዲሶችን አስመረቀ

341

ኢዜአ ታህሳስ 1/2012 በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ስር የሚገኘው የኢትዮጵያ መርከብ ሙያተኞች ማሰልጠኛ ተቋም 43 የመርከብ መሃንዲሶችን አሰልጥኖ ዛሬ አስመርቀ።

በምረቃው ስነስርዓት ወቅት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ፍሬው ተገኘ እንደገለጹት ተቋም በዓለም ደረጃ ተወዳዳሪ የሰው ኃይል እያፈራ ለገበያ በማቅረብ ሀገሪቱን ተጠቃሚ እያደረገ ይገኛል።

እስካሁንም ከአንድ ሺህ 500 በላይ ሙያተኞችን አሰልጥኖ በማስመረቅ በዓለም ላይ በሚገኙ የመርከብ ድርጅቶች እያስቀጠረ መሆኑን አመልከተዋል።

ለመሰልጠን የሚገቡትም የመካኒካልና የኤሌክትሪክ ኢንጅነሪንግ ዘርፍ የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው መሆናቸው ተወዳዳሪነታቸው እንዲያጨምር አድርጓል።

አሁን ላይ ለ18ኛ ጊዜ  43 የመርከብ መሃንዲሶች እንዲሁም ከመከላከያ ሚኒስቴር የባህር ሃይል መምሪያ የመጡ ሁለት ሰልጣኞችን  ለስምንት ወራት በማሰልጠን ማስመረቁን አስታውቀዋል።

በመርከብ ሙያ የሚሰማሩት ተመራቂዎችን በየሄዱበት በራሳቸው ተማምነው የሀገር ኩራት መሆናቸውን በማመን የሚጠብቃቸውን ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ ዶክተር ፍሬው መልዕክታቸውን  አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ማሪታይም ማሰልጠኛ ተቋም ማኔጅንግ ዳይሬክተር ሚስተር ጆሰን ያሆዲን በበኩላቸው “ተመራቂዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚጠበቀውን የመርከበኞች አቅምና ችሎታ ያሟሉ ናቸው” ብለዋል።

ይህም የመርከብ ሙያ በረጅም ጊዜ የውቅያኖስ ጉዞ የሚያጋጥመውን የአየን ንብረት መለዋወጥ ተቋቁሞ የሚፈለገውን ግብ ለመምታት የሚያስችል ነው።

ታማኝነትን፣ ቁርጠኝነትንና ብቃትን የሚየጠይቅ የሙያ ዘርፍ መሆኑን ገልጸዋል።

በተቋሙ የሚሰጠው የመርከብ ሙያተኞች ስልጠናም በንድፈ ሃሳብና በተግባር የታገዘ በመሆኑ ሰልጣኞች ዓለም አቀፍ የመርከብ እውቀት፣ ክህሎትና ስነምግባርን የተለባሱ እንደሆኑ መረጋገጡን አስረድተዋል።

ተመራቂዎች   በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚጠበቀውን የመርከበኞች አቅምና ችሎታ በማሟላት የመርከብ ሙያ በረጅም ጊዜ የውቅያኖስ ጉዞ የሚያጋጥመውን የአየን ንብረት መለዋወጥ ተቋቁሞ የሚፈለገውን ግብ ለመምታት የሚያስችል በመሆኑ ታማኝነትን፣ ቁርጠኝነትንና ብቃትን የሚጠይቅ የሙያ ዘርፍ ነው።

ተቋሙ አሰልጥኖ በውጭ አገር  ከተቀጠሩ የመርከብ ባለሙያዎች በየወሩ እስከ 350 ሺህ ዶላር የውጭ ምንዛሬ እንድታገኝ ማስቻሉን የገለጹት ደግሞ በተቋሙ የስልጠና አስተዳደርና የሰው ሃብት ማኔጀር አቶ ዘላለም ተፈሪ ናቸው።

ይህን መልካም ጅምር ለማስቀጠልም የስልጠና ዘርፎቹን ለማስፋትና የሚያሰለጥነውን የሰው ኃይል ቁጥር ለመጨመር የራሱ ህንጻ በማስገንባት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ከተመራቂዎች መካከልም ካዴት ፍስሃ ተስፋ በሰጠው አስተያየት በስልጠና ቆይታው ንድፈ ሀሰብ በተግባር የተደገፈ ዓለም አቀፍ የመርከበኞች ሙያ መቅሰሙን ገልጿል።

በቀጣይም ኃላፊነቱን በአግባቡ በመወጣት የኢትዮጵያን ክብርና ዝና ከፍ ለማድረግ  በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አመልክቷል።

በሀገር መከላከያ ሚኒስቴር የባህር ኃይል ጠቅላይ መምሪያ የመጣው ሻምበል ኸይሩ ሙደሲር በበኩሉ በቆታቸውም ዓለም አቀፍ የወታደራዊ ሳይንስና የመርከብ ሙያ እውቀት መጨበጡን ገልጿል።

ይህም  በቀጣይ በተሰማሩባቸው የስራ ቦታዎች የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት እንደሚያስችላቸው ተናግሯል።