ለተጀመረው የሰላምና የብልጽግና ጉዞ ስኬታማነት ሁሉም የድርሻውን መወጣት አለበት…አቶ ኡሞድ ኡጁሉ

70
ኢዜአ፤ ታህሳስ 1/2012 በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የተጀመረውን የሰላምና የብልጽግና ጉዞ ወደ ፊት ለማሻገር ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳዳር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ጠየቁ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያገኙት የኖቤል ሽልማት መላውን የኢትዮጵያ ህዝብ ያስደሰተና ያኮራ  ተግባር እንደሆነም ርዕሰ መስተዳደሩ ተናግረዋል። ርዕሰ መስተዳደሩ ሽልማቱን አስመልክተው ለኢዜአ እንደገለጹት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ለተጀመረው የሰላም  ግንባታና የብልጽግና ጉዞ ስኬት ሁሉም ሊረባረብ ይገባል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሀገሪቱን መምራት በጀመሩ በአጭር ጊዜ ውስጥ በሀገር ውስጥና በቀጠናው ሀገራት ያከናወኗችው የሰላም ስራዎች ውጤት ለዚህ ሽልማት ያበቃቸው መሆኑን ተናግረዋል። በተለይም ለሁለት አስርት ዓመታት ሳይፈታ የቆየውን የኢትዮ-ኤርትራ ጉዳይ ያለ ማንም አደራዳሪ እንዲፈታና የሁለቱ ሀገራት ህዝቦች የቆየ ወንድማማችነታቸው  እንዲቀጥል ማድረጋቸው የአመራር ብቃታቸው ማሳያ  መሆኑን ገልጸዋል። በተጨማሪም እርሳቸው በቀየሱት የአመራር ዘይቤና የመደመር ፍልፍና በተለይም አጋር ተብለው በሀገራቸው  ጉዳይ እንዳይወሰኑ ተገልለው የቆዩት ክልሎች በአንድ ፓርቲ ተካተው  በሀገራቸው ጉዳይ እኩል የመወሰን መብት እንዲኖራቸው ያስቻሉ መሪ ናቸውም ብለዋል ። በእርሳቸው የተጀመሩትን የሰላም፣ የብልጽግና እና የዴሞክራሲ ስራዎችን ወደፊት ለማሻገር የክልሉ መንግስትና ህዝብ ከጎናቸው መሆኑንም አስታውቀዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትናንትናው ዕለት ለተደረገላቸው የኖቬል ሽልማት የክልሉ መንግስትና ህዝብ ከፍተኛ  ደስታ የተሰማው መሆኑንም ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም