በህገ-ወጥ መንገድ 109 ሰዎችን ወደ ጅቡቲ ሲያጓጉዝ የነበረ አሽከርካሪ ተያዘ

69
ታህሳስ 1/2012 ከአማራ ክልል ባቲ ከተማ 109 ሰዎችን አሳፍሮ በህገ-ወጥ መንገድ ወደ ጅቡቲ ድንበር ሲያጓጉዝ የነበረ ከባድ የጭነት መኪና አሽከርካሪን መያዙን የአፋር ክልል ፖሊስ ኮሚሸን አስታወቀ። መኪናዉ የታየዘው ትናንት ከሌሊቱ 10 ሰአት በሰመራ ከተማ ልዩ ስሙ አይሳኢታ መገንጠያ አካባቢ መሆኑ ተገልጿል። በኮሚሽኑ ወንጀል መከላከል የስራ ሂደት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ኮማንደር መሃመድ ኡትባን እንደገለጹት የአፋር ክልል በጋላፊ በኩል ከአማራና ከትግራይ ክልሎች ለሚነሳው ህገ-ወጥ የሰዎች ዝርውውር ዋነኛ የመውጫ በር ነው። "በያዝነው በጀት አመት እስከ ህዳር ወር መጨረሻ ድረስ የአሁኖቹን ሳይጨምር ከአንድ ሺህ የሚበልጡ ሰዎች በህገ-ወጥ መንገድ ከአገር ለመውጣት ሲሞክሩ ተይዘው ወደ መጡበት እንዲመለሱ ተደርጓል"ብለዋል። ትናንትም ሌሊት ከባቲ ከተማ 109 ሰዎችን አሳፍሮ ወደ ጋላፊ ይጓዝ የነበረውና የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ3-88470 ኢት፣ የተሳቢው ደግሞ ኮድ3-26881 ኢት የሆነ ከባድ የጭነት ተሽከርካሪ በሰመራ ከተማ በአካባቢው በጸጥታ ስራ ላይ በነበሩ የክልሉ ፖሊስ አባላት መያዙን ተናግረዋል። ከተያዙት ሰዎችም ውስጥ 88ቱ ወንዶች ሲሆኑ ቀሪዎቹ ሴቶች መሆናቸውን ገልጸው ከነዚህም ውስጥ ከአሰራ ስምንት አመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች እንደሚገኙበትም ጠቁመዋል። አሸከርካሪውና የተያዙት ሰዎች በፌዴራል ፖሊስ ሚሌ ዲቪዥን ተጨማሪ ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑንም ኮማናደሩ ተናግረዋል። በኮሚሽኑ የወንጀል መከላከል ምክትል ኮሚሽነር ጣሂር መሀመድ በየክልሉቹ ያለው ቁጥጥር በቂ አለመሆንና ተያያዥ ምክንያቶች በህገ-ወጥ መንገድ የሚደረገዉን የሰዎች ዝዉዉር እንዳበራከተው ተናግረዋል። "ህገ-ወጥ የሰዎች ዝዉዉር ከፍተኛ ገንዘብና ዉስብስብ ኔትወርክ ያለበት በመሆኑ ወንጀሉን ለመካለከል የክልሉ ጸጥታ ሃይሎች ከፌዴራል ፖሊስና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰሩ ነዉ"ብለዋል። በተለይም ወንጀሉ ድንበር ተሸጋሪ በመሆኑ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር መነሻ በሆኑ ከተሞች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መስራት እንደሚገባም ጠቁመዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም