የሽልማት ስነ-ስርዓቱ የኢትዮጵያ ታሪክ በዓለም አደባባይ ጎልቶ እንዲታይ ያደረገ ነው... አቶ ንጉሱ ጥላሁን

152
ኢዜአ፤ ታህሳስ 1/2012ትናንት የተደረገው የሰላም ኖቤል ሽልማት ስነ- ስርዓት የኢትዮጵያ ታሪክ በዓለም አደባባይ ጎልቶ እንዲታይ ያደረገ ነው ሲሉ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሪታሪያት ኃላፊ ንጉሱ ጥላሁን ተናገሩ። አቶ ንጉሱ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተናገሩት ሽልማቱ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለሰላም ዘብ እንዲቆም አደራ የሰጠ መሆኑንም አክለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን በመጡ በአጭር ጊዜ ውስጥ አዲስ እሳቤ በመንደፍ ለአገራችንና ለአፍሪካ ቀንድ ሰላም አበክረው ሰርተዋል ነው ያሉት። በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል የተጋረደው የጥላቻ ግድግዳን አፍርሰው ሰላም እንዲሰፍን የሰሩት ስራ ደግሞ በዚህ ረገድ ጎልቶ የሚታይ መሆኑን አንስተዋል አቶ ንጉሱ። የጠቅላይ ሚኒስትሩ  የመደመር  እሳቤም ከአገር  ባለፈ  በዓለም አቀፍ ማህበረሰቡ ዘንድ እውቅና እየተቸረው መሆኑንም አውስተዋል። ትናንት የተደረገው የሰላም የኖቤል ሽልማት ስነ-ስርዓት የኢትዮጵያ የሰው ልጆች መገኛና ቅኝ ያልተገዛች ታሪካዊ አገር መሆኗ በዓለም አደባባይ ጎልቶ እንዲነገር ማድረጉንም አቶ ንጉሱ አብራርተዋል። በመሆኑም ሽልማቱ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ብቻ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያውያን ነው ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ አገራቸው ሲመለሱም ደማቅ አቀባባል እንዲደረግላቸው በርካታ ኢትዮጵያውያን ሲጠይቁ መቆየታቸውን አስታውሰው፤ ነገ ከቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ እስከ ቤተ መንግስት ደማቅ የአቀበባል ስነ - ስርዓት ይደረጋል ብለዋል። በስነ-ስርዓቱ ላይም ከተለያያ የህብረተሰብ ክፍሎች የተወጣጡ ግለሰቦች እንደሚገኙም ጠቁመዋል። ሽልማቱ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ዘር ቀለም ሳይለይ ለሰላምና አብሮነት የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ አደራ የሰጠ ጭምር መሆኑንም አቶ ንጉሱ በመግለጫቸው አንስተዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም