አካል ጉዳተኞች በሚፈለገው መልኩ የልማቱ ተጠቃሚ እንዲሁን በትኩረት መስራት እንደሚገባ ተጠቆመ

69
ኢዜአ ታህሳስ 01/2012  አካል ጉዳተኞች በሚፈለገው መልኩ የልማቱ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዳልሆኑ ለማስቻል በትኩረት መስራ እንደሚገባ ተጠቆመ:: የኢትዮጵያ ብሔራዊ የአካል ጉዳተኞች ኮንፌዴሬሽን ከባለድርሻ አካላት ጋር የአካል ጉዳተኛ የሥራ ዕድል ፈጠራ ከዘላቂ የልማት ግቦች አንፃር ያሉ መልካም አጋጣሚዎች ዙሪያ በአዳማ ከተማ መክሯል። የኮንፌዴሬሽኑ ስራ አስኪያጅ ወይዘሪት ድባቤ ባጫ በምክክር መድረኩ እንዳሉት ሀገሪቱ ባወጣቻቸው ህጎች መሰረት አካል ጉዳተኞች መብታቸው ተከብሮ በልማቱ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከማስቻል አንፃር ሰፊ ከፍተቶች አሉ። “ለውጥ ለማምጣት የግንዛቤ መፍጠር፣መረጃ ተደራሽ ማድረግና ንቅናቄ በመፍጠር ዙሪያ በትኩረት መስራት ይጠበቅብናል "ብለዋል። ሀገሪቱ በጀመረችው የልማት ጉዞ ውስጥ አካል ጉዳተኞች ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንዲኖራቸውና ዕኩል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ ማድረግ እንዳለባቸው ጠቁመዋል። በተለይም አካል ጉዳተኛ ሴቶች አሁንም ቢሆን ያላቸው ተሳትፎና ተጠቃሚነት አነስተኛ በመሆኑ በህብረተሰቡ ውስጥ የሚገባቸውን ቦታ እንዲያገኙ በጋራ መስራት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል። በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሴቶች ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ዓለሙ ገብሬ በበኩላቸው የአካል ጉዳተኞችን መብቶች ከማስከበር፣ተሳትፎቸውንና የመሪነት ሚናቸውን ከማስፋት እንፃር መንግስት አበረታች ሥራዎች እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል። ከፍተቶችን በማስተካከል ለአካል ጉዳተኞች እንደየችሎታቸውና ፍላጎታቸው ምቹ ሁኔታ ሊፈጠርላቸው እንደሚገባ አሳሰበዋል። በሁሉም መስኮች ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ የአስተሳሰብ ለውጥ በህብረተሰቡ ውስጥ እንዲመጣ ማስቻል ከባለድርሻ አካላት እንደሚጠበቅም ጠቁመዋል። "በማህበረሰብ መስተጋብሮች ውስጥ አካል ጉዳተኞች ያልተገደበ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ካደረግን በሀገሪቱ ልማትና ዕድገት ውስጥ ሚና ይኖራቸዋል "ብለዋል። በአዳማ ከተማ ዛሬ ለአንድ ቀን በተካሄደው የምክክር መድረክ ከተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት የተወጣጡ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።                    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም