ኢትዮጵያ የዘረመል ምርመራን ሙሉ በመሉ በአገር ውስጥ ልታካሂድ ነው

326

 ታህሳስ 01/2012 ኢትዮጵያ የዘረመል /DNA/ ምርመራን ሙሉ በሙሉ በአገር ውስጥ ልታከናውን መሆኑን ባዮቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

ኢንስቲትዩቱ ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ስምምነት ከአልያንስ ግሎባል ጋር ዛሬ ተፈራርሟል።

ስምምነቱን የፈጸሙት የኢትዮጵያ ባዮቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ካሳሁን ተስፋዬና የአልያንስ ግሎባል ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ታመር ዲግሄድ ናቸው።

ስምምነቱ በኢትዮጵያ የቀጣዩን ትውልድ የዘረመል ቅደም ተከተል መገልገያ በአገሪቱ ለማቋቋም የሚያስችል ነው ተብሏል።

የኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ካሳሁን በስምምነቱ ወቅት እንዳሉት እስካሁን በኢትዮጵያ በተለያዩ ዝርያዎች ላይ የሚካሄደው የዘረመል ምርመራ ሙሉ በመሉ በአገር ውስጥ አይከናወንም ነበር።

በስምምነቱ የዘረመል ምርመራ እስከ ማባዛት ብቻ የነበረውን የአገሪቷን አቅም ዘረመሉን እስከመለየት ያለውን ስራ በአገር ውስጥ ለመከወን ይረዳል ነው ያሉት።

ለምርምር ስራ የሚላኩ የአገር ውስጥ ዝርያዎች ይዘረፋሉ ከሚል ጥርጣሬም እንድናለን ብለዋል።

ባዮ ቴክኖሎጂ በገንዘብ፣ በእውቀትና በሰው ኃይል ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ የሚፈልግ በመሆኑ አገሪቷ ካላት አቅም አንጻር ፍላጎቱን ማሟላት አልተቻለም ብለዋል።

ውጭ አገር ተልኮ የሚካሄደው የዘረመል ምርመራ አገሪቷን ለከፍተኛ ወጪ ሲዳርግ፣ በጥራትና በፍጥነት አገልግሎት መስጠት እንዳይቻልና የአገር እድገት እንዳይፋጠን እንቅፋት ሆኖ ቆይቷል ነው ያሉት።

ስምምነቱ ችግሮቹን በማቃለል በተለይ የዘረመል ምርመራን መሉ በሙሉ በአገር ውስጥ ማከናወን ያስችላል ነው ያሉት።

በተጨማሪም ከሌሎች በባዮ ቴክኖሎጂ ላይ ከሚሰሩ ዓለምአቀፍ ኩባንያዎች ጋር በዘርፉ ለመስራት ዕድል ይፈጥራልም ብለዋል ዶክተር  ካሳሁን።

አገሪቷ ሰፊ የብዝሀ ህይወት ሃብት እንዳላት የጠቀሱት የአልያንስ ግሎባል ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ታመር ዲግሄድ በተለያዩ የባዮ ቴክኖሎጂ መስኮች ባለሙያዎችን በማሰልጠንና ዓለምአቀፍ ተሞክሮ በማጋራት ከኢትዮጵያ ጋር እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

በቅርቡ በአዲስ አበባ ቢሮ የመክፈት ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸው ይህም በባዮ ቴክኖሎጂ ዘርፍ በቅርበት ለመስራት ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥር አክለዋል።

አሊያንስ ግሎባል የፈጠራ ስራዎችና ቴክኖሎጂዎችን ለአጥኚዎች፣ ለህክምና ለሌሎች ተቋማት የማቅረብ፣ የመደገፍና የማማከር ስራ እንደሚሰራም ጠቁመዋል።

ቢሯቸው በመካከለኛው ምስራቅ፣ በአፍሪካና በኤዥያ እንደሚገኝም አብራርተዋል።

በስምምነቱ ወቅት የተገኙት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ጀማል በከር ለአንድ አገር እድገት ዋነኛው የተሻለ ምርታማነት የሚሰጥ ዝርያን በብዛትና በፍጥነት ማውጣት ነው ብለዋል።

በጤና፣ በግብርና፣ በእንስሳትና በሌሎችም የተሻለ ዝርያ በማውጣት የአገርን እድገት ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግና ስምምነቱም የአገርን ኢኮኖሚ ለማሳደግ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም