በህክምና ላይ የነበረችው ነብር ሞተች

165
ኢዜአ፤ ታህሳስ 01 / 2012  በተሽከርካሪ አደጋ በደረሰባት ጉዳት ምክንያት በመቀሌ ዩኒቨርስቲ እንስሳት ህክምና ኮሌጅ ስር በሚገኝ ሆስፒታል በህክምና ክትትል ላይ የቆየችው ነብር መሞቷን የሆስፒታሉ ሀኪም ገለፁ ። በመቐለ ዩኒቨርሲቲ የእንስሳት ህክምና ኮሌጅ የእንስሳት ህክምና ባለሙያ ዶክተር ተወልደ ፅጋብ ለኢዜአ እንደገለጡት ዩኒቨርስቲው የነብሯን ህይወት ለማትረፍ ከፍተኛ ጥረት ቢያደርግም ትናንት ማታ መሞቷን ተናግረዋል ። ነብሯ መንገድ በማቋረጥ ላይ እንዳለች በተሽከርካሪ አደጋ የአካል ጉዳት የደረሰባት ህዳር 9 ቀን 2012 ዓም ነበር ። በትግራይ ክልል ማእከላዊ ዞን ላእላይ ማይጨው ወረዳ ልዩ ስሙ ማይብራዝዮ በተባለው አካባቢ ግጭት ያጋጠማት ይህቺው ነብር በአካባቢው የመጀመሪያ ህክምና ከተደረገላት በኋላ ለተሻለ ህክምና ወደ መቀሌ የተወሰደችው ህዳር 12 ቀን 2012 ዓም ነበር ። ላለፉት 18 ቀናት በመቀሌ ከተማ ተገቢውን ህክምና ሲደረግላት ቢቆይም የሰውነቷ ግራ አካል የነርቭ ጉዳት ስላጋጠመው ህይወቷን ማትረፍ እንዳልተቻለ ዶክተር ተወልደ ተናግረዋል ። ሆስፒታሉ የኤክስሬይምርመራናየኢንፌክሽንመከላከያመድሀኒትን ጨምሮ ነብሯን ለማዳን የቻለውን ሁሉ አድርጓል ነው ሀኪሙ ያሉት ። ነብሯ በግሉኮስ ድጋፍ ባለፈው ሳምንት የማገገም አዝማሚያ አሳይታ የነበረች ቢሆንም ተጨማሪ ምግብ መውሰድ ባለመቻሏ ግን ትናንት ህይወቷ ማለፉን አስረድተዋል ። ነብሯ በሳይንሳዊ ስሟ ሊዮፓርድ ወይም የአፍሪካ ነብር መሆኑን የገለፁት በትግራይ ክልል ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ የዱር እንስሳት ባለሙያ አቶ ብርሃነ መረሳ በተለያዩ የአገራችን አካባቢዎች ከሚገኙ ሶስት የነብር ዝሪያዎች መካከል አንዷ ዝርያ ናት ብለዋል ።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም