ባዕድ ነገርን በማቀላቀል ማር ነው በማለት ሲያሰራጩ የነበሩ ግለሰቦች ተያዙ

73
ታህሳስ 01/2012በደቡብ ወሎ ዞን ኮምቦልቻ ከተማ በማር ስም ባዕድ ነገሮችን በመቀላቀል ሲያሰራጩ የነበሩ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የዞኑ ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ አስታወቀ። የመምሪያው ኃላፊ አቶ ደምስ እንድሪስ ለኢዜአ እንደገለጹት ግለሰቦች የተያዙት ትላንት ከሰዓት በኋላ ከህብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ መሰረት ፖሊስ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ባደረገው ክትትል ነው። በከተማው 03 ቀበሌ የግለሰብ ቤት ተከራይተው ባዕድ ነገሩን በማዘጋጀት ላይ የነበሩ ሦስት ሴቶችን ጨምሮ ሁለት ወንድ  ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ሊውሉ መቻላቸውን ተናግረዋል። ባዕድ ነገሩን በዋናነት የሚያቀነባብሩ ቀሪ ከሦስት በላይ ተጠርጣሪዎችን ለመያዝም ከህብረተሰቡ ጋር በትብብር እየተሰራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል። ስኳር፣ ማር መሳይ ፈሳሽ ነገርና ከውጭ አገር የሚመጣ ማር የሚያስመስል ኬምካል በመጠቀም ያዘጋጁት እንደነበረ መረጋገጡንም አስረድተዋል። ባዕድ ነገሩ በበርሚል እሳት ላይ ጥደው ከተዋህደ በኋላ አውጥተው በማቀዝቀዝ ማር ሲመስል በኩንታል ጭነው ወደ ተለያዩ አካባቢዎች ይሸጡ እንደነበርም ተረጋግጧል። "በደሴና በደቡብ ወሎ ዞን የተለያዩ ከተሞችም በባልዲ እያዘሩ ለህብረተሰቡ ይሸጡ ነበር" ያሉት ኃላፊው በጤና ላይ ከፍተኛ እንከን ሊፈጥር እንደሚችልና መጥፎ ሽታ አንዳለውም ተናግረዋል። በእለቱ አፍልተው ያረጉትና ወደ ሌላ ቦታ ሊጫን የነበረ ከሰባት ኩንታል በላይ ከባዕድ ነገር የተሰራ ማር መሰል ውህድ በቁጥጥር ስር መዋሉን ጠቁመዋል። "ግለሰቦቹ ከፍተኛ ቅንጅታዊ አሰራርና ጥንቃቄ ከማድረጋቸውም ባለፈ የአካባቢውን ማህበረሰብ መሳሪያ እያሳዩ እንገድላችኋለን በማለት ያስፈራሩ እንደነበረም ለማወቅ ችለናል" ብለዋል። በርካታ በርሜል ጥደው በእሳት እያፈሉ የሚያመርቱበትን ቤትም ለመኖሪያ ብለው የተከራዩት መሆኑን ጠቁመው "ህብረተሰቡ ቤቱን ለማንና ለምን መስሪያ እንደሚያከራይ በመለየት ህገ-ወጥ ተግባርን መከላከል ይኖርበታል"ብለዋል። የወንጀል ድርጊቱ ሲፈጸምበት የነበረው ቤት ባለንብረቶችም ቤታቸውን አከራይተው እነሱ አዲስ አበባ የሚኖሩ መሆናቸው ለተጠርጣሪዎቹ ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው ተገልጿል። ከጎረቤት የሚኖሩት ወይዘሮ ዘይነባ እሸቱ በበኩላቸዉ "ቤቱን መኖሪያ ብለው ቢከራዩትም ህገ-ወጥ ተግባር እንደሚሰሩበት ተጠራጥረናል" ብለዋል። ለጸጥታ ኃይል ለመጠቆምም ምን እንደሚሰሩ በትክክል ካለማወቃቸው ባለፈ መጠራጠራቸውን ለማንም ቢናገሩ ሙሉ ቤተሰቦቻቸውን ገድለው እንደሚሄዱ በመሳሪያ እንዳስፈራሯቸው ገልፀዋል። "ይሁን እንጂ ጥቆማ ለማድረግ ክትትልና መረጃ እያሰባሰብን ነበር" ያሉት ወይዘሮዋ አብዛኛውን ጊዜ ሌሊት እንደሚሰሩ ገልጸው መጥፎ ሽታ እንደነበረውም ተናግረዋል። በቁጥጥር ስራ የዋሉት አምስት ግለሰቦችም ጉዳያቸው በህግ እየታየ ሲሆን የተያዘው ባዕድ ነገር በጤና ላይ የሚያስከትለው ጉዳት  በባለሙያ እንደሚጣራም ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም