የኢትዮጵያና ኤርትራ ወደ ሰላም መምጣት ጠቀሜታው የጎላ ነው - አስተያየት ሰጪዎች

81
አዲስ አበባ ሰኔ15/ 2010 የኢትዮጵያና ኤርትራ ወደ ሰላም መምጣት የአገራቱን ወንድማማችነት ከማጠናከር ባሻገር ለወጪ ንግድ መስፋፋት ጠቀሜታ እንደሚኖረው ለኢዜአ አስተያየት የሰጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ተናገሩ። የሁለቱ አገሮች ወደ ስምምነት መምጣት ለኢትዮጵያ አማራጭ የባህር በር የሚያሰፋ ከመሆኑ በተጨማሪ የአገሮቹን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ግንኙነት እንደሚያሳድግ ያላቸውን እምነት ተናግረዋል። በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የጨርቃጨርቅ፤ ፋሽንና ቴክኖሎጂ ኢንስቲቲዩት መምህር አሮን ይድነቃቸው አገሮቹ ወደ ሰላም ስምምነት መምጣታቸው ለወጪ ንግድና ኢንቨስትመንት መስፋፋት ትልቅ ዕድል ይፈጥራል። ይህም ኢትዮጵያ ምርቶቿን ወደ ጎረቤት አገሮች በመላክ የምታገኘውን ገቢ ለማሳደግ እንደሚያግዛት ገልጸዋል። ወጣት ያደታ ዘሪሁን በበኩሉ አገሮቹ እስካሁን ተለያይተው መቆየታቸው ከጉዳት በስተቀር ምንም ጠቀሜታ እንዳላየበት አስተያየቱን ሰጥቷል። አሁን  ወደ ሰላም ለመምጣት እየተደረገው ያለው እንቅስቃሴ የሚበረታታና ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንደሚገባው ወጣቱ ሃሳቡን አስቀምጧል። ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ አብርሃም ክብሩ የሁለቱ አገራት ወደ ሰላም ስምምነት መምጣት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው  ይናገራሉ። የሰላም ስምምነቱ የሁለቱን አገሮች ወንድማማችነት በማጠናከር ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ግንኙነቱን ያሳድጋል ብለዋል። ሁለቱን አገሮች ወደ ሰላም ለማምጣት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ለኤርትራ ባደረጉት ጥሪ መሰረት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በጉዳዩ ላይ ለመወያየት የልዑካን ቡድን ወደ ኢትዮጵያ እንደሚልኩ መናገራቸው ይታወቃል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም