የኖቤል ኮሚቴው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ዴሞራሲያዊና ሰላማዊ ማህበረሰብ ለመፍጠር የሚያደርጉትን ጥረት ይደግፋል

87
ኢዜአ ህዳር 30/2012  የኖርዌይ ኖቤል ኮሚቴ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ ማህበረሰብ ለመፍጠር የሚያደርጉትን ጥረት ይደግፋል ሲሉ የኮሚቴው ሊቀመንበር ሚስ ቤሪት ሬስ-አንደርሰን ገለጹ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የኖቤል የሰላም ሽልማታቸውን ዛሬ በኖርዌይ ርዕሰ መዲና ኦስሎ ተቀብለዋል። የኖርዌይ ኖቤል ሽልማት ኮሚቴ ሊቀመንበር ሚስ ቤሪት ሬስ-አንደርሰን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሽልማቱን አበርክተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሽልማት ያገኙት ኢትዮጵያና ኤርትራ ያለው አለመግባባት እንዲፈታ በማድረጋቸው፣ ዴሞክራሲያዊ ስርአትን ለመገንባት እያከናወኑት ላለው ተግባር፣ በምስራቅ አፍሪካ እና በሰሜን ምስራቅ አፍሪካ ያሉ ችግሮችን በሰላምና በእርቅ እንዲፈቱ ላበረከቱት አስተዋጽኦ እንደሆነ ሊቀመንበሯ አስታውሰዋል። ለዓመታት በኢትዮጰያና በኤርትራ መካከል ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንደተቋረጠ፣ የእርስ በርስ ጦርነት እንደተካሄደና በተለያዩ ጊዜያትም ግጭቶች እንደነበሩ አውስተዋል። ይህንን ጦርነትና ሰላም አልባ የሆነ የሁለቱን አገሮች ግንኙነት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ለማስተካከል ባከናወኑት ስራ የሰላም ስምምነት መፈራረማቸውን ተናግረዋል። ''ለሰላም ስምምነቱ መፈረምና ለአገሮቹ ዳግም ግንኙነት መጀመር የኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ሚና ወሳኝ ነበር'' ብለዋል። የሰላም ስምምነቱ መፈረሙና ግንኙነታቸውን ለመጀመር ቁርጠኛ መሆናቸው ብቻ ትልቅ የሚባል ውጤት እንደሆነም ጠቅሰዋል። የሁለቱ አገሮች ህዝቦች እርስ በርስ መገናኘታቸውና ሰላም መስፈኑ እንደ ትልቅ እምርታ የሚወሰድ እንደሆነም ነው ሚስ በሪት የገለጹት። ያም ቢሆን የሰላም ስምምነቱን ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ማድረግ እንዳለባቸው ገልጸው፤ አገሮቹን የሚያገናኙ የተለያዩ የድንበር ማቋረጫዎች እንደተዘጉም አመልክተዋል። የድንበር መቋረጫዎቹ መዘጋት የሁለቱ አገሮች ህዝቦች እንቅስቃሴና ግንኙነት እንዲገደብ እንዳደረገም ጠቅሰዋል። ''የሰላም ስምምነቱ የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የባህል ልማትን ያካተተ እንደሆነና የድንበሩ መዘጋት ይሄን ስራ በሚፈለገው መልኩ እንዳይከናወን አድርጎታል'' ብለዋል። የኖርዌይ ኖቤል ኮሚቴ ከዚህ በፊት የተገኘው ስኬት እንዲሁም የዛሬው ሽልማት የሰላም ስምምነት ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ እንዲደረግ ተጨማሪ ብርታት የሚጨምር እንደሆነ ገልጸዋል። ኢትዮጵያ በአሁኑ ሰአት ዘርፈ ብዙ ፈተናዎች እንዳሉባትና ብሔርንና ማንነትን አስመልክቶ በተነሱ ግጭቶች ዜጎች ከቀዬቸው መፈናቀላቸውንም አንስተዋል። መንግስት የስራ አጥነት ችግርን በመፍታት፣ የትምህርት ተደራሽነትን ማሳደግና መሰረተ ልማትን በማስፋፋት ኢኮኖሚውን የማሳደግ ከፍተኛ ሃላፊነት እንዳለበትም ተናግረዋል። ከላይ የተጠቀሱት ስራዎች ሰላምን ለመገንባት ወሳኝ ነገሮች እንደሆኑና ሰላም ማህበራዊ ፍትህ በማረጋገጥና የኢኮኖሚ አቅምን በማሳደግ ሁሉንም ዜጎች ተጠቃሚ ማድረግን እንደሚያካትት አመልክተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በኢትዮጵያ ሰላም እንዲረጋገጥና ዴሞክራሲያዊ ስርአት እንዲገነባ የተለያዩ ስራዎችን እያከናወኑ እንደሆነ ገልጸዋል። የካቢኔያቸው 50 በመቶ ሴቶች እንዲሆኑ መደረጉ፣ የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንትና የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሴት እንዲመራው ማድረጋቸው አድናቆት የሚገባው እርምጃ እንደሆነ ገልጸዋል። ''የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ማንሳት፣ በሺዎች የሚቆጠሩ የፖለቲካ እስረኞች በመፍታት፣ የሚዲያ ነጻነት እንዲከበር የሰሩት ስራ፣ ሙስናን ለመዋጋት ያሳዩት ቁርጠኛ አቋም የሚታውስ ነው'' ብለዋል። ዘንድሮ በኢትዮጵያ የሚካሄደው ምርጫ ነጻ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ  በሆነ መልኩ እንዲካሄድ ያላቸውን ቁርጠኝነት አንስተው የምርጫው መካሄድ ኢትዮጵያ ለምታስበው እውነተኛ ዴሞክራሲ ወሳኝ እንደሆነ ተናግረዋል። የኖርዌይ የኖቤል ኮሚቴ ''ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ ማህበረሰብ ለመፍጠር የጀመሩትን ጥረት ለመደገፍ ከጎንዎት ነን እንደግፎታለን'' ብለዋል ሚስ ቤሪት። የወደፊት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ስርአትና አመራርን የሚወሰኑት ራሳቸው ኢትዮጵያውያን እንደሆኑም ገልጸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የመረጡት መንገድ ሰላምና ብልጽግናን ለኢትዮጵያ ያመጣል ብሎ ኮሚቴው እንደሚያምን ተናግረዋል። ''በሱዳን፣ በኬንያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ጂቡቲና ኤርትራ ያሉ አለመግባባቶች በሰላምና በእርቅ እንዲፈቱ በማድረግ ያከናወኑት ተግባር የሚደነቅ ነው'' ብለዋል። የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰላም ጥረት ችግሮችና ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ መፈታት እንዳለባቸው ለሌሎች የአፍሪካ አገሮች መልዕክት የሚያስተላፍ እንደሆነም አመልክተዋል። ''የኖቤል የሰላም ሽልማት ኢትዮጵያና ህዝቦቿ ሰላምን ለማምጣት ላደረጉት ጥረት እውቅና የሰጠ ነው'' ብለዋል። እ.አ.አ ለ2018 ለዓለም ሰላም መስፈን ከተሰሩ ስራዎች የጠቅላይ ሚኒስትሩ የላቀውን ድርሻ እንደሚይዝ አመልክተዋል። "ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ እንደሆነችና የሆሞ ሳፒያን ዝርያ መነሻው ከኢትዮጵያ በመሆኑ እኛ ሁላችንም ኢትዮጵያውያን ነን" ብለዋል ሚስ ቤሪት። ኢትዮጵያ በምዕራባውያን ቅኝ ያልተገዛች ልዩ አገር እንደሆነች በአፍሪካ በምታከናውናቸው ስራዎች የአፍሪካ ህብረት መቀመጫና የአፍሪካ መዲና መሆን እንደቻለችም ጠቅሰዋል። ለሰላም መስፈን የዓለም ህዝብ በትብብርና በጋራ በመስራት እንዳለባትና ጦርነቶችን አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት የሁሉም ሃላፊነትና ድርሻ እንደሆነም አሳስበዋል። የኖቤል የሰላም ሽልማቱ ከዓለም አቀፍ እውቅናው በተጨማሪ 900 ሺሕ ዶላር የገንዘብ ሽልማትም አለው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የኖቤል ሰላም ሽልማት 100ኛው አሸናፊ ናቸው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባሸነፉበት የዘንድሮው የሰላም የኖቤል ሽልማት በአጠቃላይ ለሽልማቱ 301 እጩዎች  ለዚህ ታላቅ ክብር ታጭተው የነበረ ሲሆን ከነዚህ መካከል 223 ግለሰቦችና 78 ድርጅቶች ይገኙበታል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም