ሴቶች ሰላም በማስፈን በኩል ያላቸውን የማይተካ ሚና ሊወጡ ይገባል

117
ህዳር 30/2012 ሴቶች ግጭቶችን በመከላከልና ሰላም በማስፈን በኩል ያላቸውን የማይተካ ሚና ሊወጡ እንደሚገባ ተገለጸ ። የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከኖርዌይ ቤተ ክርስቲያን የእርዳታ ድርጅት ጋር በመተባበር ''ሴቶች ለሰላም'' የሚል ኮንፍረንስ ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሂዷል። በኮንፍረንሱ መክፈቻ ላይ የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ምክትል ጠቅላይ ፀሐፊ አቶ ህሉፍ ወልደ ሥላሴ እንደገለጹት፤  በአገሪቷ ግጭቶች በሚከሰቱበት ወቅት ሴቶች፣ ህጻናትና አቅመ ደካሞች ሰለባ መሆናቸውን ጥናቶች አመልክተዋል። በሌላ በኩል ሴቶች ግጭቶችን በመከላከልና ሰላም በማስፈን በኩል የማይተካ ሚና እንዳላቸውም ገልጸዋል። አቶ ህሉፍ እንዳሉት ሴቶች ያላቸውን ችሎታ በተግባር ላይ ካዋሉት መከላከልና መፍታት የማይችሉት ግጭት የለም። በመሆኑም ''ሴቶች አቅማቸውን በተቀናጀና በተፋጠነ መልኩ ተግባር ላይ ማዋል ይገባቸዋል'' ብለዋል። የኢትዮጵያ የሐይማኖት ተቋማት ጉባዔ ሴቶች ሰላምን ለማስፈን በሚያደርጉት ጥረት ሁሉ ከጎናቸው እንደሚቆምም አቶ ህሉፍ አረጋግጠዋል። በሰላም ሚኒስቴር የሰላም ግንባታ ጄኔራል ዳይሬክተር ዶክተር ራህዋ ሙሴ በበኩላቸው ሴቶች ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የሚያስችል አቅም ቢኖራቸውም ችሎታቸውን ለመጠቀም የሚያስችል ሰፊ ዕድል አለማግኘታቸውን ገልጸዋል። ሚኒስቴሩ ሴቶች ሰላም ለማስፈን የሚጫወቱትን ሚና ለማሳደግ የተለያዩ አደረጃጀቶችን ለመፍጠር እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል። በአገር አቀፍ ደረጃ የተዘጋጀው ኮንፍረንስም ሴቶች በሰላም ዙሪያ ያላቸውን ሚና ለህብረተሰቡ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ያለመ መሆኑንም አመልክተዋል። በኮንፍረንሱ የተገኙ ተሳታፊዎችም ሴቶች በአካባቢያቸው ሰላም ለማስፈን ንቁ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል። ከአዲስ አበባ ሴቶች ማህበር የመጡት ወይዘሮ መዓዛ ዲባባ በበኩላቸው ''ከአካባቢያችን ጀምረን በአጠቃላይ በአገሪቷ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ጥረት ማድረግ ይኖርብናል'' ብለዋል። ከቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል የመጡት ወይዘሮ ካልቱባ አቡበከር እንዳሉት ሴቶች ግጭቶች በመከላካል ረገድ  ከቤታቸው ጀምሮ ሰላምን የማስፈን ሚናቸውን መወጣት አለባቸው።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም