የአማራ ብድር እና ቁጠባ ተቋም /አብቁተ/ በ13 ሚሊዮን ብር በላይ ያስገነባው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አስመረቀ

114
ኢዜአ ህዳር /2012 የአማራ ብድር እና ቁጠባ ተቋም /አብቁተ/ በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ከ13 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጭ ያስገነባውን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ፡፡ የተቋሙ የስልጠና እና ጥናት ምርምር ዘርፍ ምክትል አስፈፃሚ አቶ ተዋበ አይሸሽም በምረቃው ወቅት እንዳሉት ተቋሙ የህዝቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመፍታት የብድር እና ቁጠባ አገልግሎቶችን ይሰጣል፡፡ ተቋሙ በብድር እና ቁጠባ ከሚያገኘው ገቢ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች  ማህበራዊ አገልግሎቶችን  በማስፋፋት ሃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በዚህም በአበርገሌ ወረዳ በ13 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የፃና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታ አጠናቆ ለአገልግሎት ማብቃቱን በማሳያነት ገልፀዋል፡፡ ከትምህርት ተቋማት ግንባታ በተጨማሪም በአቅም እጥረት ምክንያት ትምህርታቸውን መከታተል ለማይችሉ 36 የሁለተኛ ደረጃና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን የገንዘብ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ የፃና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተማሪዎች መማሪያ ፣ የቤተ ሙከራ ፣ ቤተ መፅሃፍት እና የተማሪዎች እና የመምህራን መፀዳጃ ክፍሎችን ጨምሮ ስምንት ህንፃዎች ተገንብተው ለአገልግሎት መብቃታቸውን፡፡ ተቋሙ ከ27 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት በመመደብ በክልሉ የተለያዩ የልማት ስራዎች በማከናወን ላይ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ የዋግ ልማት ማህበር ዋና ዳይሬክተር አቶ ባምላኩ አበበ በበኩላቸው የዋግ ልማት ማህበር ‘’ህብረት ለዋግ ልማት‘’ በሚል መሪ ቃል በ2006 ዓ.ም ባካሄደው አገር አቀፍ የገቢ ማሰባሰቢያ ቴሌቶን መሰረት አብቁተ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለመገንባት በገባው ቃል መሰረት የተከናወነ ነው፡፡ በአብቁተ የበጀት ድጋፍ የተገነባው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በብሄረሰብ አስተዳደሩ የሚታየውን የትምህርት ተቋማት እጥረት ከመቅረፉም ባሻገር ደረጃቸውን የጠበቁ ትምህርት ቤቶችን ተደራሽ በማድረግ ትልቅ አስተዋፅኦ አለው፡፡ ልማት ማህበሩ በብሄረሰብ አስተዳደሩ የሚስተዋለውን የትምህርት ተቋማት እጥረት ከአጋር አካላት ጋር በመሆን ለመቅረፍ እየተሰራ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ባለፉት ሶስት አመታትም ከ290 በላይ የዳስ ጥላ መማሪያ ክፍሎችን ወደ ግንባታ መቀየር መቻሉን አውስተዋል፡፡ የትምህርት ቤቱ መገንባት በአካባቢው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ተደራሽ ባለመሆኑ ምክንያት የሚያቋርጡ ተማሪዎች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለማድረግ ያስችላል ያሉት ደግሞ የብሄረሰብ አስተዳደሩ ትምህርት መምሪያ ሃላፊ አቶ ገብረ ህይወት አዱኛ ናቸው፡፡ በዚህም የተገነባው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በጻና ቀበሌ እና አካባቢው የሚገኙ ከሰባት በላይ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን የሚያስተሳስር ሲሆን 210 ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተናገር የሚችል ነው። የጻና ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ አህዛ ገብረ ሃና በበኩላቸው በአካባቢያቸው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ባለመኖሩ ምክንያት ሁለት ልጆቻቸውን የአምስት ሰአት የእግር ጉዞ በማድረግ ለመማር ይገደዱ እንደነበር ገልፀዋል፡፡ አሁን ላይ በአካባቢያቸው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመገንባቱ ደስተኛ መሆናቸውን እና ለልጆቻቸው መማሪያ ያወጡት የነበረውን የገንዘብ ወጭ እንደሚያስቀርላቸው ተናግረዋል፡፡ በምረቃ ስነ ስርዓቱም ከክልል፣ ከዞንና ከወረዳ የተውጣጡ የአመራር አካላት እንዲሁም የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም