ፓርቲው ለህዝቦች እኩል ተሳትፎና ተጠቃሚነት አዲስ ተስፋ ይዞ የመጣ መሆኑን ምሁራን ገለጹ

52
ኢዜአ ህዳር 29/2012 ዓ/ም የብልጽግና ፓርቲ የኢትዮጵያ ህዝቦች በሁሉም መስኮች እኩል ተሳትፎና ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችል አዲስ ተስፋን ይዞ ያመጣ መሆኑን የወሎ ዩኒቨርሲቲ  ምሁራን ገለጸ። በዩኒቨርሲቲው የፖለቲካ ሳይንስ መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ሽመልስ ኃይሉ ለኢዜአ እንዳሉት  በኢትዮጵያ እየተካረረ የመጣው የብሔር ፖለቲካ ሀገሪቱን አጣብቂኝ ውስጥ አስገብቷል። በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ሲዘወር የነበረው ስርዓት አግላይ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አንዱ የበላይና ሌላው ደግሞ የበታች በማድረጉ ዜጎች በሀገራቸው ጉዳይ እኩል የመሳተፍ መብት እንዳልተከበረላቸው ተናግረዋል፡፡ ይህም ተከትሎ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በተፈጠረው የጸጥታ ችግርና የፖለቲካ ሽኩቻ የሰው ህይወት እንዲጠፋ፣ የአካል ጉዳትና ንብረት እንዲወድም ምክንያት ሆኗል። እንደ ምሁሩ ገለጻ አሁን የመጣው የብልጽግና ፓርቲ እነዚህና ሌሎች ውስብስብ ችግሮችን በመፍታት ዜጎች በሀገራቸው ጉዳይ በእኩል ተሳታፊነት እንዲወስን ያስችላል። ለውጡን በማስቀጠል የበለጸገችና ሉአላዊነቷ የተከበረ ሃገር ለመገንባት ጉልህ ሚና እንደሚኖረውም አመልክተዋል። በዩኒቨርሲቲው የሰላምና ልማት ትምህርት ክፍል መምህር  ረዳት ፕሮፌሰር ሰብስብ አዲስ በበኩላቸው የብልጽግና ፓርቲ ዜጎች በሀገራቸው  ተዘዋውረው  ሰርተው እራሳቸውንና ሌላውን ለመጥቀም የሚያስችል ፕሮግራም ይዞ መምጣቱን  ተናግረዋል። ቀደም ሲል ይስተዋል የነበረውን የሴራ ፖለቲካና የልዩነት አባዜ ዜጎች በሚኖሩበት አካባቢ ሃብት እንዲፈጥሩ ሳይሆን አንዱ ሌላውን የሚጠራጠርበት እንደነበር አውስተዋል። የብልጽግና ፓርቲ ባመጣው ለውጥ  ህብረተሰቡ አብሮነቱንና እሴቱን በማጎልበት በሀገራዊ ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ጉዳዮች  በፍትሃዊነት የሚጠቀምበት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ገልጸዋል። "የፓሪቲውን መርህ፣ ደንብና አሰራር በተከታታይነት ግልጽ በማድረግ ህዝቡ በለውጡ ተማምኖ እንዲቆምና ለቀጣይነቱ እንዲታገል ማድረግ ወቅቱ የሚጠይቀው ጉዳይ ነው" ብለዋል። በማንኛውም ጊዜ ለውጥ ሲመጣ ተገፋን የሚሉ ኃይሎች የማደናገርና የማደናቀፍ እኩይ ሴራ መስራታቸው ስለማይቀር መንግስት ጉዳዩን ሳይንቅ በውይይትና በድርድር ማተካከል እንደሚገባውም ጠቁመዋል። የብልጽግና ፓርቲ ስህተቶችን በማረም  የኢትዮጵያ ህዝቦች በሁሉም መስኮች እኩል ተሳትፎና ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችል አዲስ ተስፋን ይዞ መምጣቱን  ከፕሮግራሙ መረዳት እንደሚቻል ምሁራኑ በሰጡት አስተያየት  አብራርተዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም