ፊንላንድ በኢትዮጵያ ለሚካሄደው አገራዊ ምርጫ የሚውል የ800 ሺህ ዩሮ ድጋፍ ልታደርግ ነው

583

ኢዜአ ህዳር 29/2012 የፊንላንድ መንግስት  በኢትዮጵያ ለሚካሄደው አገራዊ ምርጫ የሚውል የ800 ሺህ ዩሮ ድጋፍ ልታደርግ ነው።

የድጋፍ ስምምነቱን በኢትዮጵያ የፊንላንድ አምባሳደር ሚስ ሄለና አይራክሲነንና የተባበሩት መንግስታት ደርጅት የልማት ፕሮግራም የኢትዮጵያ ተወካይ ቱርሀን ሳሌህ ተፈራርመዋል።

የፊንላንድ መንግስት የ800 ሺህ ዩሮ ድጋፉ በኢትዮጵያ ጠንካራ የዴሞክራሲ ስርአትን ለመገንባት ምርጫዎችን በሚደግፍ ፕሮጀክት(ሲድስ ፕሮጀክት) ላይ ለሚሰሩ ስራዎች የሚውል ነው።

ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ፣ ተአማኒና ግልጽ ምርጫ እንዲካሄድና ከምርጫው በፊት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን አቅም ለማጠናከር ድጋፍ ማድረግ እንደሆነ በአዲስ አበባ ከሚገኘው የፊንላንድ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በኢትዮጵያ የፊንላንድ አምባሳደር ሚስ ሄለና አይራክሲነን በዘንድሮው ዓመት የሚካሄደው አገራዊ ምርጫ ለኢትዮጵያ የወደፊት ሁኔታ ወሳኝ ሚና ይኖረዋልም ብለዋል።

ፊንላንድ ምርጫው ሰላማዊና ተአማኒ እንዲሆን በምታደርገው ድጋፍ ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።