የሳዑዲ ዓረቢያ የንግድ ልዑካን ቡድን ኢትዮጵያን እየጎበኘ ነው

77
ኢዜአ ህዳር 29 / 2012 ዓ.ም ኢትዮጵያን እየጎበኘ ያለው የሳዑዲ ዓረቢያ የንግድ ልዑካን ቡድን በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ባለብዙ ዘርፍ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያሸጋግረው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ። በሳዑዲ ዓረቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አብዱልአዚዝ ካታሊ የተመራው የንግድ ልዑካን ቡድን ትናንት ምሽት ነው አዲስ አበባ የገባው። 50 አባላት ያሉት የንግድ ልዑካን ቡድን ዛሬ ይፋዊ የስራ ጉብኝቱን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጀምሯል። ከልዑካን ቡድኑ መካከል 28ቱ የሳዑዲ ዓረቢያ መንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ሲሆኑ 22ቱ ከግሉ ዘርፍ የተውጣጡ ናቸው። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሒሩት ዘመነ ከሳዑዲው አቻቸው አብዱልአዚዝ ካታሊ ጋር በሁለቱ አገራት ባለብዙ ዘርፍ ግንኙነት ላይ መክረዋል። ባለስልጣናቱ በአገራቱ መካከል ያለውን የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ለማጠናከር ባቋቋሙት የጋራ ኮሚሽን የተያዙ አጀንዳዎች ላይ በሰፊው መወያየታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ነቢያት ጌታቸው ገልጸዋል። በአገራቱ ነባራዊ ሁኔታዎችና የጋራ ኮሚሽኑ በሚጠናከርበት ሁኔታ ላይ መምከራቸውንም ተናግረዋል። እንደ ቃል አቀባይ ነቢያት ገለጻ የሳዑዲ ዓረቢያው የንግድ ልዑካን ቡድን ጉብኝት የአገራቱን ባለብዙ ዘርፍ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋግረዋል። የልዑካን ቡድኑ በሦስት ቀናት የኢትዮጵያ ቆይታው ከተለያዩ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ጋር እንደሚወያይ ይጠበቃል። እንደ አውሮጳዊያኑ ዘመን አቆጣጠር 1948 የተጀመረው የኢትዮጵያና የሳዑዲ ዓረቢያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አሁን ላይ በንግድ፣ በኢንቨስትመንትና በተለያዩ ዘርፎች ቀጥሏል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም