ኢትዮጵያ አበረታች ቅመሞችን በመከላከል ስራ ተጨባጭ ለውጥ አምጥታለች — የዓለም አትሌቲክስ

433

ኢዜአ ህዳር 29 / 2012 ዓ.ም ኢትዮጵያ አበረታች ቅመሞችን ለመከላከል ባከናወነችው ተግባር ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት እንደቻለች በዓለም አትሌቲክስ የተመሰረተው የአትሌቲክስ ኢንተግሪቲ ዩኒት ገለጸ።
የአትሌቲክስ ኢንተግሪቲ ዩኒት አበረታች ቅመሞችን ለመከላከልና ፍትሃዊ ውድድር እንዲኖር ለማድረግ በዓለም አትሌቲክስ የተቋቋመ ነው።

ይህ የአትሌቲክስ ኢንተግሪቲ ዩኒት ለሁለት ቀናት የሚቆይ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ በአዲስ አበባ እያካሄደ ይገኛል።

የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኩ በዋናነት በጎዳና ላይ ሩጫዎች አበረታች ቅመሞችን የመጠቀም ዝንባሌዎችን ለመከላከል ያለመ ነው።

በዝግጅቱ የተገኙት የአትሌቲክስ ኢንተግሪቲ ዩኒት ምክትል ኃላፊ ቶማስ ካፕዲቪያል እንዳሉት ኢትዮጵያ አበረታች ቅመሞችን ለመከላከል እየሰራችው ያለው ስራ የሚበረታታ ነው።

ከአራት ዓመት በፊት በኢትዮጵያ በኩል አበረታች መድሃኒትን እንደ ችግር በማየት ለመከላከል የሚሰራ ምንም አይነት እንቅስቃሴ አልነበረም።

ከሶስት ዓመት ወዲህ ግን ችግሩን ለመከላከል የራሱን ጽህፈት ቤት በማቋቋም እየተሰሩ ባሉ ስራዎች ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት ችላለች።

ይህ ግን የአንድ ጊዜ ስራ ብቻ ሳይሆን ተከታታይነት ባለው መልኩ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል ምክትል ኃላፊው።

በቀጣይም አሁን እየተሰሩ ካሉ ስራዎች በተጨማሪ አትሌቶች አበረታች ቅመሞች እንዲጠቀሙ የሚገፋፉ አካላትን የመለየትና ከምንጩ ለማድረቅ መስራት ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ምክትል ተቀዳሚ ፕሬዚዳንት አትሌት ደራርቱ ቱሉ ኢትዮጵያ ከአበበ ቢቂላ ዘመን ጀምሮ ትልቅ ታሪክ የሰራችበት አትሌቲክስ እንዳይበላሽ ሁሉም ኃላፊነቱን እንዲወጣ ነው ያሳሰበችው።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ፀረ አበረታች ቅመሞች ጽህፈት ቤት ዳይሬክተር አቶ መኮንን ይደርሳል የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ኢንተግሪቲ ዩኒት በጎዳና ላይ ሩጫ ተወዳዳሪዎች የሚታየውን ችግር ለመቅረፍ የሚሰራውን ስራ ኢትዮጵያም የምትደግፈው ሀሳብ ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ በኩል አበረታች ቅመሞች በመጠቀም ቅጣት የተላለፈባቸው በጎዳና ላይ ውድድር ተካፋይ የነበሩ አትሌቶች ናቸው።

ይህ የሆነው ቀደም ሲል በጎዳና ውድደሮች የሚካፈሉ አትሌቶች ላይ ይደረግ የነበረው የአበረታች ቅመሞች ምርመራ ዝቅተኛ በመሆኑ እንደነበረ ገልጸዋል።

ይህን ችግር ለመፍታት ኢትዮጵያ ከአትሌቲክስ ኢንተግሪቲ ዩኒት ጋር በመተባበር በጽህፈት ቤቱ በኩል በእቅድ ደረጃ የተቀመጡ ስራዎች እንደሚሰሩም ተናግረዋል።

በጎዳና ላይ ሩጫዎች አበረታች ቅመሞችን የመጠቀም ዝንባሌዎችን መከላከልን ዓላማ ባደረገው መድረክ ከ20 ያላነሱ የአትሌት ማናጀር ተወካዮች ና ከ100 በላይ አትሌቶች ይካፈላሉ።