በኢትዮጵያ ግብርናን ከኢንዱስትሪ ጋር ለማስተሳሰር የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ የ945 ሚሊዮን ብር ብድር ከጣሊያን ተገኘ

68
አዲስ አበባ ሰኔ 15/2010 በኢትዮጵያ ግብርናን ከኢንዱስትሪ ጋር ለማስተሳሰር የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ የ945 ሚሊዮን ብር ብድር ጣሊያን ሰጠች። ገንዘቡ ከ30 እስከ 40 ዓመታት ውስጥ ተከፍሎ የሚጠናቀቅ እንደሆነ የብድር ስምምነቱ ዛሬ በአዲስ አበባ በተፈረመበት ወቅት ተገልጿል። በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አድማሱ ነበበና በኢትዮጵያ የጣሊያን አምባሳደር ሚስተር አርቱሮ ሉዚ መካከል የብድር ስምምነቱ ፊርማ ተከናውኗል። ሚኒስትር ዴኤታው አቶ አድማሱ ነበበ እንደገለጹት፤ የሁለቱ አገሮች የብድር ስምምነት በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች የግብርናውን ዘርፍ ከኢንዱስትሪው ጋር ለማስተሳሰር ለሚደረገው ጥረት ድጋፍ የሚሆን ነው። አገሪቱ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን በግብና ዘርፍ የያዘችውን ዕቅድ ለማሳካት፣ ግብርናውን ለማዘመንና ከኢንዱስትሪው ጋር ለማስተሳሰር የተገኘው ብድር ከፍተኛ እገዛ እንደሚኖረው ጠቁመዋል። በኢትዮጵያ የጣሊያን አምባሳደር አርቱሮ ሉዚ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ያለውን የግብርና ዘርፍ ለማዘመን መንግስታቸው ትኩረት የሚሰጥ እንደሆነ ገልጸዋል። አገራቸው ቀደም ሲል በኢትዮጵያ በተለይም በትምህርት፣ በገጠር ልማት፣ በጤና፣ በእናቶችና ህጻናት ድጋፍ እንዲሁም የማህበራዊ ድጋፍ ስራዎችን ለመደገፍ ጥረት ስታደርግ መቆየቷል ተናግረዋል። በቀጣይም ኢጣሊያ ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥልና ለኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ የሚውል 22 ሚሊዮን ዩሮ ብድር ለመስጠት ቃል ገብተዋል አምባሳደር አርቱሮ። የዛሬው የሁለቱ አገሮች የድጋፍ ስምምነት ባለፈው ዓመት የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመንና የገጠር ልማት ግቦችን ለማሳካት ካስቀመጧቸው የትኩረት አቅጣጫ አንዱ መሆኑ ተነግሯል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም