ማዕከሉ የተሻለ ምርት የሚሰጡ የሰሊጥና የማሾ ዝርያዎችን በማሰራጨት አርሶ አደሩን ተጠቃሚ እየደረገ ነው

69
ሁመራ ሰኔ15/2010 የሑመራ እርሻ ምርምር ማዕከል በሽታና ድርቅን ተቋቁመው የተሻለ ምርት የሚሰጡ የሰሊጥና የማሾ ዝርያዎችን ለአርሶ አደሮች በማሰራጨት ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን አስታወቀ። ማዕከሉ በምርምር ያገኛቸውን የሰሊጥና የማሾ ዝርያዎች ተጠቅመው በሄክታር እስከ 12 ኩንታል ምርት እያገኙ መሆናቸውን የአካባቢው አርሶ አደሮች ገልጸዋል። የማዕከሉ ዳይሬክተር አቶ ገብረኪሮስ ማሩ ለኢዜአ እንዳሉት በእንስሳት ሃብት፣ በሰብል ልማት፣ በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና በዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂ ስርጭት ላይ ማዕከሉ የተለያዩ የምርምር ሥራዎችን እያከናወነ ነው። በማዕከሉ ምርምር ከተካሄደባቸው የቅባት ምርቶች መካከል የሰሊጥ ምርታማነትና ጥራትን ለመጠበቅ የተካሄደው ምርምር ይገኝበታል። በእዚህም ሰቲት አንድ፣ ሁለትና ሦስት የተባሉ የሰሊጥ ዝሪያዎችን ከማዕከሉ በምርምር በማውጣት ለአካባቢው አርሶ አደሮች ሲያሰራጭ መቆየቱን ዳይሬክተሩ ለኢዜአ ተናግረዋል። ማዕከሉ ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ ባካሄዳቸው የምርምር ሥራዎች የተገኙ የሰሊጥ እና ማሾ በመባል የሚታወቀው የጥራጥሬ ምርት በሽታና ድርቅን በመቋቋም የተሻለ ምርት የሚሰጡ መሆናቸውን አስረድተዋል። በመሆኑም በአከባቢው አርሶ አደሮች ዘንድ ለዘር ተማራጭ መሆናቸውን ነው የገለጹት። በትግራይ ምዕራባዊ ዞን የቃፍታ ሑመራ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ገብረእግዚአብሔር ተጫነ እንዳሉት ቀደም ሲል በባህላዊ መንገድ የተመረቱ የሰሊጥ ዝርያዎችን ሲጠቀሙ በሄክታር አራት ኩንታል ምርት ብቻ ያገኙ እንደነበር አስታውሰዋል። ካለፈው ዓመት ጀምሮ ከማዕከሉ በምርምር የተገኙት የሰሊጥ ዝርያዎችን መጠቀም በመጀመራቸው በሄክታር 11 ኩንታል የሚጠጋ ምርት ማግኘት መጀመራቸውን ተናግረዋል። በምርምር የተገኘው ዘር ድርቅና በሽታንን ተቋቁሞ የተሻለ ምርት የሚሰጥ ሆኖ እንዳገኙትም አርሶ አደሩ አስረድተዋል። እንደ አርሶ አደሩ ገለጻ በዘንድሮ የመኸር እርሻ የተሻለ ምርት ለማግኘት አቅደው ከማዕከሉና ከዘርፉ ባለሙያዎች ጋር ተባብረው እየሰሩ ይገኛሉ። " ከማዕከሉ ያገኟቸውን የሰሊጥና የማሾ ዝርያዎች በመጠቀም የተሻለ ምርት ለማግኘት የሚያስፈልጉ የግብርና ግብአቶችን ለመጠቀም ተዘጋጅቻለሁ " ያሉት ደግሞ ሌላው የወረዳው ነዋሪ አርሶ አደር አልጋነሽ ገብረእግዚአብሔር ናቸው። ምርጥ ዘሮችን በመስመር በመዝራት፣ ማዳበሪያ በመጠቀምና ማሳቸውን ደጋግመው በማረስና በማለሳለስ የተሻለ ምርት ለማግኘት መዘጋጀታቸውንም ተናግረዋል። ባለፈው የምርት ዘመን ከሄክታር ያገኙትን 7 ኩንታል የሰሊጥ ምርት ዘንድሮ ወደ 10 ኩንታል ከፍ ለማድረግ ማቀዳቸውንም ተናግረዋል። በቃፍታ ሑመራ እርሻና የተፈጥሮ ሃብት ልማት መምሪያ የስነ አዝርእት ባለሙያ አቶ ገብረመስቀል ብርሃነ በበኩላቸው የሑመራ እርሻ ምርምር ማዕከል በየዓመቱ በምርምር የሚያወጣቸውን ምርጥ ዘሮች ተቀብለው ለሞዴል አርሶ አደሮች እንደሚያሰራጩ አመልክተዋል። በተያዘው የ2010/11 የምርት ዘመንም ከአንድ ሺህ 700 ኩንታል በላይ ምርጥ የማሾና የሰሊጥ ዝርያዎችን ወደአርሶ አደሮች እንደሚያደርሱ ገልጸዋል። ምርጥ ዘሮችን ከማሰራጨት ባለፈ የተለያዩ ሙያዊ ድጋፎችን ለማድረግ ዝግጅት በማድረግ ላይ መሆናቸውንም አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም