ኢትዮጵያዊያን አብረው የኖሩ፣ የተጋቡና የተዋለዱ የማይነጣጠሉ ሕዝቦች ናቸው - ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ

81
ኢዜአ ህዳር 28/2012 ኢትዮጵያዊያን ባስ ለመጠበቅ በአንድ ፌርማታ የተሰባሰቡ ሕዝቦች ሳይሆኑ አብረው የኖሩ፣ የተጋቡና የተዋለዱ፣ የማይነጣጠሉ፤ በሠላም ጊዜ ግን የሚኳረፉ ሕዝቦች ናቸው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተናገሩ ። 14ኛው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ሕዝቦች በዓልን አስመልክቶ የተዘጋጀ ሲምፖዚየም ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሂዷል። በሲምፖዚየሙ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ "ኢትዮጵያዊያን አብረው የኖሩ፣ የተዋለዱ፣ የተጋቡ፣ በጋራ የተጋደሉ፣ በአንድ ጉድጓድ የተቀበሩና በችግር ጊዜ የማይነጣጠሉ፤ በሠላም ጊዜ ግን የሚኳረፉ ሕዝቦች ናቸው" ሲሉ ተናግረዋል። "ኢትዮጵያውያን ጦርነት፣ ረሃብና ችግር ሲነሳ የሚተባበሩ ናቸው" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያን የትብብር ልምምድ ኢትዮጵያን ለማበልጸግና ለማሻሻል ከደገሙት የበለጸገች ኢትዮጵያን መፍጠር ይቻላል ብለዋል። በመሆኑም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች አብሮ ለመኖርና ለማደግ የሚያስችሏቸውን መልካም ነገሮች በማጉላት መመካከር ይገባልም ብለዋል። ኢትዮጵያ በባህል፣ በቋንቋና በትውፊት ሀብታም በመሆኗ ይህንን በማስተማር መቻቻልን ማዳበር እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል። ዴሞክራሲን ያልጀመሩትና ያልተለማመዱት አገራት በጣም ከባድ ያደርገዋል ያሉት ሚኒስትሩ በኢትዮጵያም ያልተለመዱ ንግግሮችና ባህሪዎች ይታያሉ ብለዋል። "በመሆኑም ስንጀምረው ከባድ ቢሆንም ትከሻችንን በማስፋት ብንተባበርና ብንቻቻል፣ ዴሞክራሲን መሰረት ብናደርግ ለትውልድ የበለጸገች ብቻ ሳይሆን የዴሞክራሲ ስርዓት ያላት ኢትዮጵያን መፍጠር ይቻላል" ነው ያሉት። ኢትዮጵያ በድህነትና በልመና ያለች አገር መሆኗ ሐቅ በመሆኑ ማመንና ወደ ብልጽግና ለመሸጋገር እንድንትበቃ ከክፋት፣ ከምቀኝነት፣ ከጥላቻና ከቁርሾ በመውጣት ለልማት በጋራ መስራት እንደሚገባም አሳስበዋል። የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ለዘመናት የታገሉት በኢትዮጵያ አብሮ ለመኖር ብቻ ሳይሆን በእኩልነት ሁሉም ለፍቶ ጥሮ የሚኖርባት፣ አንዱ እየበላ ሌላው የበይ ተመልካች የማይሆንባት አገር ለመፍጠር እንደነበርም አውስተዋል። እንዲሁም ሁሉም ዜጋ በብቃቱ ተወዳድሮ መስራት፣ መምራት፣ ማግኘት፣ በነጻነት መንቀሳቀስ የሚችልባትን ኢትዮጵያ ለመፍጠር እንደሆነም ዶክተር አብይ አክለዋል። ይህ እንዳይሆን ሲደረግ የነበረው ማንኛውም ሙከራ ኢትዮጵያን ወደኋላ ያስቀረ አደገኛ መሆኑን ተረድቶ ይህን ተግባር በማስቀረት አገሪቱን ለማበልጸግ በጋራ መኖርና ለአፍሪካ ኩራት መሆን ይገባናል ብለዋል። ከ10 ዓመት በኋላ አሁን ያለው ድንቁርና፣ ኋላቀርነት ጠፍቶ የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመፍጠር ዛሬ መሰረት የሚጣልበት በመሆኑ ሠላምን፣ መቻቻልን፣ አብሮነትና የወንድማማችነት ትሩፋት አብሮ ለመስራትና ለመጠቀም ቃል የሚገባበት ሊሆን ይገባልም ነው ያሉት። የመከላከያ ሠራዊቱም ከማነኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ገለልተኛ በመሆን አገሪቷ የጀመረችውን የብልጽግና ጎዳና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ መሰረት ለማስያዝ የሚወሰዱ ማንኛውንም ሁኔታዎች መስዋዕት ለመሆን ዝግጁ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል። የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም በበኩላቸው ጥቃቅን ልዩነቶችን ወደ ጎን በመተው ለአገሪቱ ህልውናና ለህዝቦቿ ዋስትና መቆም እንደሚገባ ተናግረዋል። በአገሪቷ ውስብስብ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ችግሮች ተደቅነዋል በመሆኑም እነዚህን ችግሮች በመፍታት አገሪቷን ወደ እድገት ሊያመጡ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ ማተኮር ይገባል ብለዋል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም