በመንግስት ድጎማ የሚቀርበው የስኳር ምርት በመቋረጡ ተቸግረናል....የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች

71
ኢዜአ ህዳር 28 ቀን 2012 በመንግስት ድጎማ የሚቀርበው የስኳር ምርት ላለፉት ሁለት ወራት በመቋረጡ መቸገራቸውን የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡ የከተማው አስተዳደር በበኩሉ የስኳር ስርጭቱ እንዲስተጓጎል ያደረገው ወኪል ድርጅት ውሉ ተቋርጦ በሌላ አከፋፋይ እንዲተካ መደረጉን ገልጿል፡፡ የከተማው ነዋሪ ወይዘሮ ሙሉነሽ ካሳ በመኖሪያ አካባቢያቸው ከሚገኝ ነጋዴ በኩፖን ይገዙት የነበረው ስኳር ላለፉት ሁለት ወራት በመቋረጡ ከግለሰብ ነጋዴ ኪሎውን በ60 ብር ለመግዛት መገደዳቸውን ተናግረዋል። በከተማው የሽንታ አካባቢ ነዋሪ ወይዘሮ እቴናት መንግስቱ በበኩላቸው " በቤተሰብ ልክ በየወሩ የተመደበልኝን አራት ኪሎ ስኳር ከመስከረም ወር ጀምሮ ተቋርጦብኛል" ብለዋል፡፡ መንግስት በ23 ብር ሒሳብ የሚሸጠውን አንድ ኪሎ ስኳር በአሁኑ ወቅት ከነጋዴዎች በ50 ብር በመግዛት ለአላስፈላጊ ወጪ መዳረጋቸውንም አስረድተዋል፡፡ "በርካታ ቤተሰብ አለኝ፤ በየወሩ እስከ 10 ኪሎ ስኳር እጠቀማለሁ፤ አሁን ግን በቀበሌ የሚሰራጨው ስኳር ላለፉት ሁለት ወራት በመቋረጡ ተቸግሪያለሁ።" ያሉት ደግሞ የአራዳ ክፍለ ከተማ ነዋሪ አቶ ታምራት ደሴ ናቸው፡፡ የስኳር ስርጭቱ በመቋረጡ በወር ለስኳር የሚያወጡት ከ230 ብር ወደ 460 ብር ማድጉንና በእዚህም ለአላስፈላጊ ወጪ መዳረጋቸውን ተናግረዋል፡፡ የጎንደር ከተማ አስተዳደር ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ አምሳሉ ደረጀ በበኩላቸው የከተማው ህብረተሰብ ያቀረበው ቅሬታ ትክክል መሆኑን አምነዋል፡፡ " ላለፉት ሁለት ወራት ስርጭቱ የተቋረጠው ከስኳር ፋብሪካዎች ምርቱን ተረክቦ ለከተማው እንዲያሰራጭ ውል የገባው ድርጅት በውሉ መሰረት ስራውን በአግባቡ ባለማከናወኑ ነው " ብለዋል፡፡ የችግሩ ምንጭ ሲጠና ድርጅቱ ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ ከመንግስት ጋር የገባውን ውል እንዲቋረጥ ተደርጓል" ያሉት አቶ አምሳሉ፣ በአሁኑ ወቅት የስኳር ስርጭቱ በቀድሞው ጅንአድ በኩል የሚጀመርበት ሁኔታ መመቻቸቱን ተናግረዋል፡፡ የተቋረጠው የስኳር ስርጭት በቀጣዩ ሳምንት እንደሚጀምር ገልጸው፣ "ስርጭቱም በከተማው በተቋቋሙ 1ሺህ 732 ቸርቻሪ ነጋዴዎች አማካኝነት ወደ ህዝቡ እንዲደርስ ይደረጋል"ብለዋል፡፡ እስከዛሬ በየወሩ ከ8ሺህ ኩንታል በላይ ስኳር ለጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ሲሰራጭ እንደነበር ኃላፊው አስታውሰዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም