በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን የሶስት 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ግንባታ ተጠናቀቀ

57
ነቀምቴ ሰኔ 15/2010  በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ከ25 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ ግንባታቸው የተጠናቀቁ ሶስት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች  ለአገልግሎት መዘጋጀታቸውን የዞኑ ትምህርት ቤቶች ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡ የጽህፈት ቤቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ታሪኩ ከበደ እንደገለፁት የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ በመደበው በጀት ግንባታቸው በ2008 ዓ.ም ተጀምሮ አሁን የተጠናቀቁት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በአባቦ ጉዱሩ፣ በሆሮ፣ እና በጮመን ጉዱሩ ወረዳዎች የሚገኙ ናቸው ፡፡ ትምህርት ቤቶቹ በ2011 የትምህርት ዘመን ከ1 ሺህ 440 በላይ ተማሪዎችን ተቀብለው የመማር ማስተማር ስራቸውን ለመጀመር የውስጥ ቁሳቁስ በማሟላት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል ። በአባቦ ጉዱሩ ወረዳ የቁብሣ ቅዳሜ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ተፈራ ታደሰ በሰጡት አስተያየት የትምህርት ቤቱ ግንባታ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የተገዙ ቁሳቁሶች በቦታው መድረሳቸውን ገልፀዋል፡፡ በተመሳሳይ በሆሮ ወረዳ የበቀለ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ተመስገን ዳባ በበኩላቸው የትምህርት ቤቱ ግንባታ ተጠናቆ በአሁኑ ጊዜ የውስጥ ቁሳቁሶች መረከባቸውን አስረድተዋል ። የአባቦ ጉዱሩ ወረዳ የቢፍቱን ኑፍ ባቴ ቅዳሜ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ገለታ ተመስገን በሰጡት አስተያየት ትምህርት ቤቱ በአከባቢያቸው መገንባት ቀደም ሲል ልጆቻቸው የሁለተኛ ደረጃ ትምህር ቤት ፍለጋ በየቀኑ ከ12 እስከ 24 ኪሎ ሜትር የሚያደርጉትን አድካሚ ጉዞ እንደሚያስቀርላቸው ገልፀዋል፡፡ የሆሮ ወረዳ የቡርቅቱ ኦበራ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ገመቹ አብዲሣ በበኩላቸው  በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በአከባቢያቸው አለመኖር ትምህርታቸውን አቋረጠው ቤት የሚቀመጡ ልጆች ወደ ትምህርት ቤት እንዲመለሱ የሚያደርግ በመሆኑ መደሰታቸውን ገልፀዋል ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም