ዩኒቨርሲቲዎች ከዕውቀት መገብያ ባሻገር የአብሮነት መለማመጃ ማዕከል ናቸው---ፕሮፌሰር ሒሩት ወልደማርያም

73

ህዳር 28 ቀን 2012 ዩኒቨርሲቲዎች ከእውቀት መገብያ ባለፈ የእርስ በእርስ ትስስርና አብሮነት መለማመጃ ማዕከል መሆናቸውን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትሯ ፕሮፌሰር ሒሩት ወልደማርያም ገለጹ፡፡

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ "አንድ ተማሪ ለአንድ ቤተሰብ" በሚል ፕሮጀክት በተቋሙ የተመደቡ ተማሪዎችን ከጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ጋር ለማስተዋወቅ የቃል ኪዳን ቤተሰብ መተዋወቂያ መድረክ አካሂዷል፡፡

ሚንስትሯ በመድረኩ ላይ እንዳሉት በአገሪቱ የመጀመሪያ የሆነው የቃልኪዳን ቤተሰብ ምስረታ ተማሪዎች ባይተዋርነት ሳይሰማቸው ለትምህርታቸው ትኩረት እንዲሰጡ የሚያደርግ መልካም ተግባር ነው፡፡

ዘመድና ቤተሰብን ማስፋት ለማህበራዊ መስተጋብርና ውጤታማነት የላቀ ጥቅም እንደሚኖረው ጠቁመው፣ "ፕሮጀክቱ ከዩኒቨርሲቲው አልፎ እንደ አገር የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን የሚያጠናክር ነው" ብለዋል፡፡

ዜጎች እርስ በርስ እንዲከፋፈሉ ለሚያደርጉ ኃይሎች የያዙት ዓላማ በኢትዮጵያ ህዝቦች አንድነት የሚከሽፍ መሆኑን የሚገነዘቡበት ፕሮጀክት መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

"ይህን የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተግባርና ተሞክሮ በመቀመር በሌሎች የአገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎችም እንዲሰፋ ይደረጋል" ሲሉም ሚንስትሯ ገልፀዋል፡፡

በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ዕውቀትን ከመገብየት ባለፈ የአብሮነትና የእርስ በርስ ትስስር መለማመጃ መሆናቸውንም አመልክተዋል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕርግ የአማራ ክልል ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ መላኩ አለበል በበኩላቸው "የፕሮጀክቱ ዓላማ ከግብ እንዲደርስ የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል" ብለዋል፡፡

በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ባሉ ዩኒቨርሲቲዎች ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲኖር የክልሉ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።

በኦሮሚያ ክልል በፀጥታ ስጋት ምክንያት ትምህርታቸውን ትተው ለመጡ የክልሉ ተወላጅ ተማሪዎችም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ዘላቂ መፍትሄ እንዲሰጥም ጠይቀዋል፡፡

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አስራት አፀደወይን በበኩላቸው "ፕሮጀክቱ ተማሪዎቹ በትምህርት ቆይታቸው ከስጋት ነጻ ሆነው እንዲማሩ ከማድረግ ባለፈ የአካባቢውን ወግና ልምድ እንዲያውቁ የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል"፡፡

ተማሪዎችን የሚረከቡ የቃል ኪዳን ቤተሰቦችም ለስጋ ልጆቻቸው የሚያደርጉትን ድጋፍና እንክብካቤ ለቃል ኪዳን ልጆቻቸውም በመስጠት ውጤታማ እንዲሆኑ የሚደግፉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

"ፕሮጀክቱ በከተማው ማህበረሰብና በተማሪዎች መካከል ጥብቅ ቤተሰባዊ ትስስር በመፍጠር አሁን እየተሸረሸረ ለመጣው ኢትዮጵያዊ አንድነት እንዲጠናከር መፍትሄ ይሆናል" ብለዋል፡፡

ፕሮጀክቱ በዚህ ሳይወሰን እያደገ የሚሄድና የሚቀጥል መሆኑን የገለጹት ደግሞ የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባና የዩኒቨርሲቲው ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ ኢንጂነር ማስተዋል ስዩም ናቸው፡፡

የቃል ኪዳን ቤተሰቦቹ ዩኒቨርሲቲው የሰጣቸውን አደራ በመቀበል ልጆቻቸው በትምህርት ቆይታቸው ውጤታማ እንዲሆኑ ያላሰለሰ ድጋፍ እንዲያደርጉ አስገንዝበዋል፡፡

ከቃል ኪዳን ቤተሰቦች መካከል አቶ አስፋው በሪሁን ዛሬ የተረከቧትን ልጅ ከሥጋ ልጆቻቸው ሳይለዩ ለማስተማርና ከቁም ነገር ለማብቃት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልፀዋል።

ከቃል ኪዳን ልጃቸው ብቻም ሳይሆን ከስጋ ወላጆቿ ጋር ጥብቅ ቁርኝት ለመፍጠር እንደሚሰሩም ተናግረዋል፡፡

"የእዚህ ፕሮጀክት የመጀመሪያ ተጠቃሚ በመሆኔ እድለኛ ነኝ" ያለው ደግሞ ተማሪ ዮናስ ፈይሳ ነው፡፡

በትምህርት ቆይታው የሚያጋጥመውን ችግር በቅርብ ላሉት የቃል ኪዳን ቤተሰቦቹ በማማከርና ድጋፍ በማግኘት ትምህርቱን ያለ ስጋት መማር ማቀዱን ተናግሯል፡፡

በመድረኩ ላይ የፌደራል፣ የክልልና የዞን ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ታዋቂ ኮሜዲያንና አርቲስቶች ተገኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም