ዩኒሳ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎችና የተለያዩ ተቋማትን የሰው ኃይል አቅም እየገነባ ነው

123

ኢዜአ ህዳር 28 ቀን 2012 በአዲስ አበባ የሚገኘው የደቡብ አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ማዕከል ዩኒሳ የዩኒቨርሲቲዎችና የተለያዩ ተቋማትን የሰው ኃይል አቅም እየገነባ መሆኑ ተገለጸ።

ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን 71 ተማሪዎችን ትናንት በዶክትሬት፣ በማስተርስና በመጀመሪያ ዲግሪ አስመርቋል።

ከተመራቂዎቹ መካከል 61 የዶክትሬት፣ ስድስት የማስተርስ እና ቀሪዎቹ የመጀመሪያ ዲግሪ ትምህርታቸውን የተከታተሉ ናቸው። ሳይንስ፣ ምንድህስና፣ ቴክኖሎጂ፣ ግብርናና አካባቢ ሳይንስ፣ ጤና፣ ሥነ-ባህሪይ፣ ህግ እና ቢዝነስ አስተዳደር ተመራቂዎቹ የሰለጠኑባቸው የትምህርት መስኮች ናቸው።

የማዕከሉ ዳይሬክተር ዶክተር ፅጌ አበራ በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው ማዕከሉን በኢትዮጵያ መክፈቱ በተለይም የዶክትሬት ፕሮግራም ተመራቂዎች ቁጥር እንዲጨምር ዕድል ፈጥሯል።

ከምሩቃኑ መካከል አብዛኞቹ በመንግሥት ድጋፍ የተማሩ የዩኒቨርሲቲ ሌክቸረሮች መሆናቸውም ፕሮጀክቱ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎችን የሰው ኃይል አቅም እየገነባ መሆኑን እንደሚያሳይ ተናግረዋል።

አብዛኞቹ ምሩቃን በመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች፣ በፍትህና በጤና መስኮች እንዲሁም መንግስታዊና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች አመራሮች መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በዩኒቨርሲቲው የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ምክትል ዲን ዶክተር ሞክጎቡ ፋሶኤን ማዕከሉ እ.አ.አ የ2004 የኢትዮጵያና ደቡብ አፍሪካ የትምህርት ትብብር ስምምነት ውጤታማነት ማሳያ ነው ብለዋል። ስምምነቱን መነሻ በማድረግ እ.አ.አ. 2007 የደቡብ አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ "ዩኒሳ" ማዕከሉን በኢትዮጵያ በይፋ ከፍቶ የአቅም ግንባታ ስራውን የጀመረበትን ሁኔታም አስታውሰዋል። ይህ ለአገሪቷ ሁለንተናዊ ዕድገት ግብዓት የሆነውን የሰው አቅም የመገንባት የሁለትዮሽ ትብብር ቀጣይነት እንዳለውም አስታውቀዋል። የደቡብ አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ማዕከል "ዩኒሳ" የትምህርት ፕሮግራሞችን ተደራሽ ከማድረግ ባሻገር የዶክትሬትና የማስተርስ ዲግሪ ተመራቂዎችን የጥናትና ምርምር ወጪ ይሸፍናል። የኬሚስትሪና ፊዚክስ ተመራቂዎች ለመመረቂያ ጥናታቸው የተሟላ የቤተ-ሙከራ አገልግሎት እንዲያገኙም ወደ ደቡብ አፍሪካ ይልካል። ዩኒቨርሲቲው ትናንት ለዘጠነኛ ጊዜ ተማሪዎችን ያስመረቀ ሲሆን እስካሁን በዶክትሬት 286፣ በማስተርስ 340 እና በመጀመሪያ ዲግሪ 125 ተማሪዎችን በአዲስ አበባ በሚገኘው ማዕከሉ አስመርቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም