በደሴ ከተማ ሶስተኛው የስፖርት ፌስቲቫል ተካሄደ

76
ኢዜአ ህዳር 27/2012 በደሴ ከተማ "በአካል ብቃት እንቅስቃሴ በንክኪ የማይተላለፉ በሽታዎችን እንከላከል" በሚል ሀሳብ የተዘጋጀ ሶስተኛዉ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ስፖርት ፌስቲቫል ተካሄደ። በፌስቲቫሉ  ወጣቶች፤ የወሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና ሌሎችም የከተማው ነዋሪዎች ተሳትፈውበታል። ዛሬ ከጧቱ 12 ሰዓት እስከ ረፋዱ ሶስት  ሰዓት የተለያዩ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ተደርጓል። የደሴ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ  አቶ አበበ ገብረመስቀል በዚህ ወቅት እንዳሉት በከተማው ከአሁን ቀደም  የጎዳና ላይ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ቢጀመርም በተለያዩ ምክንያቶች መቀጠል አልቻለም፡፡ አሁን የተጀመረው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንዲቀጥል ከተማ አስተዳደሩ የድርሻውን እንደሚወጣ ገልጸዋል። "የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎችን በማመቻቸት በየወሩ ሁሉም ህብረተሰብ በጋራ እንዲሰራ፣  ጤናውንና ሰላሙን እንዲጠብቅም እንሰራለን" ብለዋል፡፡ የአስተዳደሩ  ባህል ቱሪዝም ስፖርት መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ሰይድ አራጋዉ በበኩላቸው የስፖርት እንቅስቃሴ ወጣቱን ከሱስ ከማላቀቅ ባለፈ እርስ በእርስ እንዲተዋወቅ የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል። እንቅስቃሴው የነቃ የህብረተሰብ ክፍልና አምራች ዜጋ ለመፍጠርም ጉልህ ሚና እንደሚነረው አመልክተዋል። ከፌስቲቫሉ ተሳታፊዎች መካከል ወጣት ሽመልስ አለሙ  በጎዳና ላይ በሚመቻቹ የስፖርት እንቅስቃሴዎች  በመሳተፍና በጎደኞቹ ግፊት በሂደት ከሱሰኝነት ነጻ መሆኑን  ገልጿል፡፡ በዚህ ፌስቲቫል ብቻ ሳይሆን ዘወትር  ጠዋት ጠዋት ለአንድ ሰዓት ያህል ስፖርት በመስራት ጤንነታቸውን መጠበቅ እንደቻሉ የተናገሩት ደግሞ  ሌላው የፌስቲቫሉ ተሳታፊ ወይዘሮ ሙሉ አህመድ ናቸው። ፌስቲቫሉ  ደቡብ ወሎ ዞንና ደሴ ከተማ አስተዳደር በጋራ ያዘጋጁት ሲሆን በእንቅስቃሴው ከአምስት ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም