ጉባኤው ሕብረተሰቡ የሰብዓዊ መብቶች መከበር ላይ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርግ ጥሪ አቀረበ

68
ኢዜአ ህዳር 27/2012  የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ ሕብረተሰቡ የሰብዓዊ መብቶች መከበር ላይ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርግ ጥሪ አቀረበ። ጉባኤው ባለፉት አመታት ያደረገውን የትግል ጉዞና የአለም የሰብዓዊ መብቶች ቀን ላይ ያተኮረ ውይይት ዛሬ በአዲስ አበባ አካሄዷል። የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ ከተለያዩ ዘርፎች በተውጣጡ 32 ባለሙያዎችና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በ1984 ዓ.ም መቋቋሙ ይታወሳል። የጉባኤው ነባር አባል አቶ አበበ ወርቄ እንደገለጹት ጉባኤው የተመሰረተው ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት መዳበር፣ ለህግ የበላይነት መስፈንና ለሰብዓዊ መብቶች መከበር ነው። ሆኖም ባለፉት አመታት ጉባኤው "ለተቋቋማበት ዓላማ እንዳይንቀሳቀስና ጭራሹኑ ለማፍረስ በመንግስት አካላት ከፍተኛ ጫና ሲደረግበት ቆይቷል" ብለዋል። በጉባኤው አባላትና በጉባኤው የሰብዓዊ መብት ጥሰት መርማሪዎች ላይም እንግልት፣ ግድያ፣ ከአገር መሰደድና ሌሎች ጉዳቶች እንደደረሰባቸውም አቶ አበበ ገልጸዋል። አሁን ግን የጉባኤውን የውስጥ አደረጃጀት ለማጠናከር፣ ገጽታ ለመገንባትና አቅም ለማጠናከር ስትራቴጂ ተዘጋጅቶ እየተሰራ መሆኑን ነው የገለጹት። በመሆኑም ዜጎች በጉባኤው ስር በተቋቋሙ ኮሚቴዎች ውስጥ አባል በመሆን የበኩላቸውን ሚና እንዲያበረክቱ ጥሪ አቅርበዋል። ከጉባኤው መስራቾችና ነባር አባላት አንዱ የሆኑት ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም እንደተናገሩት ጉባኤው ህልውናውን እንዳያጣና እንዳይፈርስ "በርካታ አባላት እስከ ህይወት ማጣት የደረሰ መሰዋትነት ከፍለውበታል"። በቀጣይም ጉባኤው መልሶ እንዲያንሰራራና እንዲቋቋም ዜጎች የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉ አሳስበዋል። ሌላው የጉባኤው ነባር አባል አቶ አምሃ መኮንን "ቀደም ሲል በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በኩል ለጉባኤው አዎንታዊ አመለካከት እንዳልነበረ" አንስተዋል። በቅርቡ ኮሚሽኑ ላይ ከተከናወኑት ለውጦች በኋላ  ግን በጋራ ለመስራት የሚያስችል ሁኔታ መፈጠሩን ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ በበኩላቸው በአገሪቷ ተግባራዊ ከተደረገው ለውጥ ጋር ተያይዞ በሰብአዊ መብቶች መከበር ላይ መሻሻሎች መኖራቸውን ተናግረዋል። ሆኖም አሁንም ብዙ ክፍተቶችና ቀሪ ስራዎች መኖራቸውን ገልጸው፤ እነዚህ ችግሮችን ለመፍታት ሁሉም የህብረተሰብ አካላት ንቁ ተሳትፎ ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል። ኮሚሽኑን በአዲስ መልክ ለማደራጀት እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ዶክተር ዳንኤል፤ ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጋር በቅርበት ለመስራት ፍላጎትና ዝግጁነት መኖሩንም ጠቁመዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም