ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ህብረት 170 ሚሊየን ዩሮ ድጋፍ አገኘች

54
ኢዜአ ህዳር 27/2012 የአውሮፓ ሕብረት ኢትዮጵያ በጤና፣ በስራ ዕድል ፈጠራ፣ በኢንቨስትመንትና በሌሎችም መስኮች ለምታከናውናቸው ተግባራት አቅም ግንባታ የሚውል የ170 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ አደረገ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በቅርቡ የአውሮፓ ሕብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ሆነው የተሾሙትን ሚስ ኡርሱላ ቮን ደር ሌይን በጽህፈት ቤታቸው አነጋግረዋል። ሕዳር 21 ቀን 2012 ዓ.ም ኮሚሽኑን ለመምራት ከተሾሙ ቀዳሚ ጉብኝታቸውን በኢትዮጵያ ያደረጉት ፕሬዝዳንቷ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለኢትዮ-ኤርትራ ሰላም መምጣት የተጫወቱትን ሚና አድንቀዋል። የ2019 የሰላም የኖቤል አሸናፊ በሆናቸውም የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል። ኢትዮጵያ ላለፉት ዘመናት ለቅኝ ግዛት ሳትንበረከክ ሉዓላዊቷን አስጠብቃ መቆየቷን አድንቀው፤ በአሁኑ ወቅት የጀመረችውን አገራዊ ለውጥም ለመደገፍ ቁርጠኝነታቸውን አረጋግጠዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በበኩላቸው ፕሬዝዳንቷ ቀዳሚ ጉብኝታቸውን በኢትዮጵያ ማድረጋቸውን አድንቀው፤ ሕብረቱ ለኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ የልማት አጋር መሆኑን አስታውሰዋል። ሕብረቱ ድጋፉን ወደፊትም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ያላቸውን እምነት በመግለጽ፤ በተለይም አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻሻያ ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያሻው ለፕሬዝዷንቷ አስረድተዋል። የአፍሪካና የአውሮፓ ሕብረት ትብብር ተጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ። ሕብረቱ ለኢትዮጵያ ያደረገው የ170 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍም ለጤናው ዘርፍ ማሻሻያ፣ ለስራ ዕድል ፈጠራና ለኢንቨስትመንት ማስፋፊያ፣ ለምርጫ ቦርድ አቅም ግንባታና አገር በቀል ኢኮኖሚ እንደሚውል ተገልጿል። ሕብረቱ ለኢትዮጵያ የለገሰው ገንዘብ ከዚህ በፊት ሲያደርጋቸው ከቆዩ ድጋፎች የላቀ መሆኑም ተጠቁሟል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም