በኢትዮጵያ ለትራፊክ አደጋ ችግሮችና መፍትሄዎች የሚያመላክት አገራዊ የመንገድ ደህንነት ጥናትና ምርምር ማዕከል ሊኖር ይገባል ተባለ

130
ኢዜአ ህዳር 26/2012 በኢትዮጵያ ለትራፊክ አደጋ ችግሮቻችን መፍትሄዎችን የሚያመላክት አገራዊ የመንገድ ደህንነት ጥናትና ምርምር ማዕከል ሊኖር እንደሚገባ ተገለጸ። ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በትራፊክ ደህንነት ላይ በጥናትና ምርምር የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ በማሳደግ ማህበራዊ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡም ጥሪ ቀርቧል። የትራንስፖርት ሚኒስቴር  “ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ከማረጋገጥ አኳያ ያላቸው ሚና” በሚል ርዕስ  ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር ዛሬ መክሯል። የትራንስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሙሉ ገብረእግዚአብሔር በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት “እንደ አገር ለትራፊክ አደጋ ችግሮቻችን መፍትሄዎችን የሚያመላክት አገራዊ የመንገድ ደህንነት ጥናትና ምርምር ማዕከል የለንም” ብለዋል። ማዕከሉ ባለመኖሩ ደግሞ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በዘርፉ የሚያደርጓቸውን ጥናትና ምርምር ውጤቶች ለግብአት እንዳይውሉ እንደዳረገና የቅንጅት አሰራር ክፍተት መፍጠሩንም ገልጸዋል። የትምህርት ተቋማቱ ችግሮችን ለመፍታት የሚያደርጉትን የተናጥል ጥረት አቀናጅተው እንዲሰሩ በማድረግ ላይ ሚኒስቴሩን ጨምሮ ዘርፉን የሚመሩ አካላት ድክመት ነበረብን ብለዋል። መንግስትም በቀጣይ የጥናትና ምርምር ማዕከሉ ሊቋቋም በሚችልበት ሁኔታ ላይ በትኩረት እንደሚመለከተውና በጉዳዩ ዙሪያ የበኩሉን ድርሻ እንደሚወስድም አመልክተዋል። ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋርም በትብብር እንደሚሰራም ተናግረዋል። ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በትራፊክ ደህንነት ላይ በጥናትና ምርምር የሚያደርጉትን አስተዋጽኦም በማሳደግ ማህበራዊ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡም ሚኒስትር ዴኤታዋ ጥሪ አቅርበዋል። የሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ዲን ዶክተር በለው ዳኘው የትራፊክ ደህንነትን አስመልክቶ ዩኒቨርሲቲው ጥናትና ምርምሮች ቢያደርግም መሬት ወርዶ እንዳይሰራበት በዘርፉ በዩኒቨርስቲና ኢንዱስትሪ ያለው ትስስር ደካማ እንደሆነ ገልጸዋል። የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የጥናትና ምርምር ስራዎችን እንዲያግዙ የዩኒቨርሲቲና ኢንዱስትሪ ትስስሩም ማጠናከር ይገባል ብለዋል። ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በበኩላቸው በዘርፉ ጥናቶች ለመጠቀም ቅንጅታዊ የአሰራር ስርአትና አደረጃጀት መፍጠር እንደሚገባቸው ተናግረዋል። ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በትራፊክ ደህንነት ላይ ማህበራዊ ሃላፊነታቸውን ለመወጣት በጋራ መስራት እንዳለባቸውም አመልክተዋል። ሌሎች ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትም ለዘርፉ ግብዓት የሚሆኑ የጥናት ውጤቶች እየተሰሩ ቢሆኑም ሚኒስቴሩን ጨምሮ የትራንስፖርት ዘርፉ እኛን በችግሮቹ ዙሪያ እያሳተፈን አይደለም ብለዋል። ዛሬ የተደረገው ውይይት ስለትራፊክ ደህንነት ግንዛቤ “እንደርሳለን!” በሚል ለተጀመረው የህዳር ወር አገራዊ ንቅናቄ አካል ሲሆን በውይይቱ ላይ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ የፖሊስ እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል:: የ1 ሚሊዮን ገደማ የተሽከርካሪ ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ የ7 ሚሊዮን ተሽከርካሪ ካላት ግብጽና 3 ሚሊዮን ባለቤት ከሆነችው ኬንያ በላይ ከፍተኛ አደጋ እንደሚመዘገብባት ተጠቁሟል። የ“ግሎባል በርደን ኦፍ ዲዚዝ” ጥናት እንዳመላከተው እ.አ.አ በ2030 ማላሪያ በ24 በመቶ ሲቀንስ፤ የመንገድ ትራፊክ ደህንነት አደጋ ደግሞ በ112 በመቶ ይጨምራል የሚል ትንበያውን አስቀምጧል። በአገራችን የዘመናዊ ትራንስፖርት አገልግሎት መሰጠት ከተጀመረ 112 ዓመት እንደተቆጠረ መረጃዎች ያመለክታሉ። ከ85 እስከ 95 በመቶ ለአለማችን የመንገድ ትራፊክ አደጋ መንስኤው ከሰዎች ባህሪ ጋር ተያይዞ ሲሆን  አገራችንን ጨምሮ ከሠሐራ በታች ችግሩ ገዝፎ እንደሚታይም ጥናቶች ያሳያሉ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም