የተሽከርካሪ አደጋ መዘዝ ከአካላዊና ስነ ልቦናዊ ቀውስ እስከ ሕይወት ቅጥፈት

65

ኢዜአ-ህዳር 26 ቀን 2012 በኢትዮጵያ የተሽከርካሪ አደጋ ከአካላዊና ስነ ልቦናዊ ቀውስ እስከ ሕይወት ቅጥፈት የሚያደርስ የእለት ተዕለት ትዕይንት ሆኗል።

በ19ኛው ዓመቱ የተሽከርካሪ አደጋ ጉዳት ሰለባ የሆነው ወጣት አበራ ፈቃዱም መጻኢ ተስፋቸውን ከተቀሙ ወጣቶች መካከል ተጠቃሽ ነው።

ከአንድ መቶ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ እንዳላት በምትገመተው ኢትዮጵያ አጠቃላይ የተሽከርካሪዎች ብዛት አንድ ሚሊዮን እንደማይሞላ ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት።

አገሪቷ በተሽከርካሪዎች ብዛት በጣም ዝቅተኛ በሚባል ደረጃ ብትገኝም በታዳጊዋ አገር ህዝብ ላይ በየዕለቱ የሚደርሰው የተሽከርካሪ አደጋ የታዳጊዎችን ብሩህ ተስፋ እያጨለመ፣ ለጉዳይ የወጡትን መንገድ ላይ እያስቀረ፣ ከልሂቅ እስከ ደቂቅ ሕልውናቸውን እየነጠቀ ይገኛል።

ዘርፈ ብዙ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ግጭቶች ባልተላቀቋት አገር የተሽከርካሪ አደጋ ተጨማሪ መዘዝ ዜጎች ጥረው ግረው ካፈሩት ንብረት ውድመት በላይ አካላዊና ስነ ልቦናዊ ቀውስ እስከ ሕይወት ነጠቃ መባባሱ አገራዊ ጉዳቱን አሳሳቢ አድርጎታል።

በተሽከርካሪ አደጋ ምክንያት በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ለሞት ይዳረጋሉ።

በቅርቡ የፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን ባወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በአገሪቷ በየዕለቱ በዚሁ አደጋ 12 ሰዎች ይሞታሉ።

ለአብነትም በ2010 ዓ.ም በደረሰ የትራፊክ አደጋ የ5 ሺ 118 ሰዎች ሕይወት አልፏል፤ ከ7 ሺ 400 በላይ ሰዎች ለከባድ ጉዳት፣ ከአራት ሺ በላይ ሰዎች ደግሞ ለቀላል የአካል ጉዳት ተዳርገዋል።

በ2010 እና በ2011 ዓ.ም የደረሰው የሀብትና ንብረት ውድመቱም ከ179 ቢሊዮን ብር በላይ ይገመታል።

በአገሪቷ በርካታ ዜጎችን ለሞትና ለአካል ጉዳት የዳረገውና ለንብረት ውድመት ምክንያት የሆነው የተሽከርካሪ አደጋ ሰለባ ከሆኑ ወጣቶች መካከል አንዱ አበራ ፈቃዱ ነው።

የሱልልታ ከተማ ነዋሪው አበራ የቀን ስራውን እያከናወነ ነበር ትምህርቱን የሚከታተለው።  ሐምሌ 2011ዓ.ም አገር አማን ብሎ በችግኝ ተከላው ስራ ላይ በነበረበት ያላሰበው አደጋ አጋጥሞታል።

ወጣት አበራ የተሽከርካሪ አደጋ ከተከሰተበትና በእግሮቹ ላይ ጉዳት ከደረሰበት በኋላ “እየሰራ እማራለሁ፤ ነገን እደርስበታለሁ” የሚለው ምኞቱ  ከስኬት ማማ ላይ ሳይደርስ የወላጆቹ ጥገኛ ሆኗል።

የአደጋ ሰለባ የሆነው ወጣት በ”እኔ ላይ የደረሰው በሌሎች ላይ አይድረስ” በማለት ጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጠው አጥብቆ ይጠይቃል።

ውስብስብ የትራፊክ አደጋ በግለሰብ፣ በቤተሰብና አገር ላይ ከፍተኛ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶችን እያስከተለ ይገኛል።

ልክ እንደ አበራ ሁሉ በየዕለቱ የተሽከርካሪ አደጋ ሰለባ በመሆን ሆስፒታል የሚደርሱ፣ ለወላድ እናቶች የሚቀርብን ደም በትልቁ የሚሻሙ፣ አካላቸውን የሚያጡት ቁጥራቸው ብዙ ነው።

በአቤት ሆስፒታል የህክምና ጥራትና የህሙማን ፍሰት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ዮናስ ከፈለኝ፤ በየዕለቱ ወደ ሆስፒታሉ የሚመጡትን የአደጋው ሰለባዎች በመጥቀስ ነው የችግሩን ስፋት የሚያመላክቱት።

ይህ እየባሰበት የመጣው የተሽከርካሪ አደጋ መንስኤዎች ዘርፈ ብዙ መሆናቸውን ይገልጻሉ። በተለይም የአሽከርካሪዎች ቸልተኝነት ትልቁን ድርሻ ይወስዳል ባይ ናቸው።

ችግሩ ከሁሉም አካላት ሃላፊነት ጉድለት የሚደርስ በመሆኑም አሳሳቢውን ችግር ለማቃለል ሁሉም አካል ሃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ ነው የሚናገሩት።

በሌላ በኩል በመንጃ ፈቃድ አሰጣጥና በአሽከርካሪዎች ብቃት ጉዳይ ላይ የሚመለከተው መንግስታዊ አካል ተገቢውን ቁጥጥር ሊያደርግ እንደሚገባም አስተያየታቸውን ይናገራሉ።

በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የመንገድ ደህንነት ባለሙያ ኢንስፔክተር አሰፋ መዝገቡም፤ የአደጋው መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ መምጣቱን ያምናሉ።

ለአደጋው መከሰት መንስኤዎቹ በርካታ ቢሆኑም በፍጥነት ማሽከርከር ትልቁን ድርሻ እንደሚይዝ ኢንስፔክተሩ ይገልጻሉ።

ችግሩን ለመቀነስም ፍጥነት ላይ የሚሰረው የራዳር ቁጥጥሩ መልካም ጅማሮ መሆኑን ገልጸው፤ ጅምሩንም ችግሩ በሚከሰትባቸው ቦታዎች በማስፋት ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

በርካታ የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋማት በአሽከርካሪዎች ብቃትና መንጃ ፈቃድ አሰጣጥ ላይ ቅሬታዎች ሲነሱባቸው ይስተዋላል።

በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን የጠየቅናቸው የሮሆቦት የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋም ባለቤት አቶ አምሳሉ አምባው፤ በስልጠና አሰጣጡ ዙሪያ በተቻለ መጠን ብቃት ያላቸውን አሽከርካሪዎች ለማፍራት እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ በ2012 ዓ.ም በሶስት ወራት ብቻ በርካታ የህይወት፣ የአካልና የንብረት ውድመት ተከስቷል።

ለእነዚህ አደጋዎች በምክንያትነት የሚቀመጡት ደግሞ የእግረኛና የአሽከርካሪ ስህተት በዋናነት ሲጠቀሱ፤ በመንገድና በተሽከርካሪ የቴክኒክ ችግሮች የሚከሰቱ አደጋዎችም ድርሻቸው ቀላል አይደለም።