የወላይታ የሶዶ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል የኩላልት እጥበት ህክምና ጀመረ

53
ኤዜአ ህዳር 26/2012 የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ቲቺንግና ሪፌራል ሆስፒታል የኩላልት እጥበት ህክምና መሰጠት መጀመሩን አስታወቀ። የሆስፒታሉ የቀዶ ህክምና ስፔሻሊስት ዶክተር ጌታሁን ሞላ እንደገለጹት የኩላልት ችግር ብዙዎችን ለስቃይና ለሞት እየዳረገ ነው። በተለይም በአካባቢው በኩላልት ችግር ወደ ሆስፒታሉ የሚመጡና ወደ አዲስ አበባ የሚላኩ ታካሚዎች በከፍተኛ ሁኔታ እየተበራከቱ መጥተዋል። ህክምናው ደግሞ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ በመሆኑ የማህበረሰቡን ችግር ለማቃለል ታስቦ ሆስፒታሉ ወደ ተግባር መገባቱን ተናግረዋል። እንደሀገር በዘርፉ የግብአትና የሰለጠነ የሰው ኃይል ማሟላት አስቸጋሪ ቢሆንም መንግስት ከዞን እስከ ፌዴራል ድረስ ባደረገው ርብርብ ህክምናው መጀመር እንደቻሉ አስረድተዋል። ዶክተር ጌታሁን የዘርፉ ህክምና ውድ ቢሆንም  የህብረተሰቡን ችግር ለማቃለል መጠነኛ የሆነ ክፍያ በመጠየቅ መርዳታቸውን እንደሚቀጥሉ ጠቁመው የሚመለከታቸው አካላት ድጋፍ ማድረግ እንደሚበቅባቸውም አሳስበዋል፡፡ የዘርፉ ህክምና የደረሰበት ደረጃ የሚመጥን ዘጠኝ ያህል ማሽኖች ከጀርመን ሃገር በማስመጣት በቀን ሶስት ፈረቃ በአማካይ እስከ ዘጠኝ ሰዎችን ማከም የሚያስችል ህክምና በይፋ መጀመራቸውን አስታውቀዋል። በሆስፒታሉ የኩላልት እጥበት ህክምና ክፍል አስተባባሪ አቶ ጌታሁን ታደሰ በበኩላቸው “ሆስፒታሉ የኩላልት እጥበት ህክምና በተደራጀ መልኩ እየሰጠ ነው “ ብለዋል፡፡ አሁን ላይ ሆስፒታሉ እንደ አቅጣጫ ትኩረት እየሰጠ ያለው በድንገተኛ አደጋዎች ጉዳት ለደረሰባቸው እንደሆነ ጠቅሰው በቀጣይ እስከ ንቅለ ተከላ ድረስ መስጠት የሚያስችል አደረጃጀት እንዳለውም ተናግረዋል። እንደ አቶ ጌታሁን ገለጻ ህክምናውን ከጀመረ ወዲህ 78 ዜጎች አገልግሎቱን አግኝቷል፡፡ ድንገት በደረሰባቸው አደጋ ኩላሊታቸው ተጎድቶ በአቅራቢያቸው ህክምናው መሰጠት በመጀመሩ ለመታከም መምጣታቸውን የተናገሩት ደግሞ አቶ ደምሴ ደስታ የተባሉ ታካሚ ናቸው። ህክምናው በቅርበት መጀመሩ ሩቅ ሄደው ለመታከም የሚጠይቃቸው ከፍተኛ ወጪና እንግልት እንደሚያቃልልላቸው ተናግረዋል፡፡ ሌላው ታካሚ ወይዘሮ አስቴር አንበሴ በበኩላቸው ህክምናውን ሀዋሳና አዲስ አበባ በመመላለስ ከጀመሩ ከአንድ ዓመት በላይ እንደሆናቸው ገልጸዋል። ከገንዘቡም በላይ ለመታከም ሲመላለሱ ለሌላ በሽታ የመጋለጥና መጉላላት ሲገጥማቸው እንደነበር ጠቅሰው በአቅረቢያቸው የአገልግሎቱ መጀመር ችግራቸውን ለማቃለል እንደረዳቸው ተናግረዋል። በአቅራቢያቸወ አገልግሎቱ እንዲጀመር አስተዋጽኦ ላደረጉ ሁሉ ምስጋናቸውንም አቅርበዋል። ሆስፒታሉ ከአንድ ዓመት በፊት የኩላልት እጥበት ህክምና እንደሚሰጥ ኢዜአ በወቅቱ ዘግቧል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም