ህግና ስርዓትን ያልተከተለ የጸረ አረም ኬሚካል ርጭት ወደ ድህነት እየከተተን ነው - ንብ አርቢዎች

148

ኢዜአ፤ ህዳር 26/2012 በትግራይ ክልል ህግና ስርአት ባልተከተለ መንገድ የሚረጨው ፀረ አረም ኬሚካል ወደ ድህነት እየከተተን ነው ሲሉ ንብ አርቢዎች ቅሬታቸውን ገለፁ ።

በክልሉ ምስራቃዊ ዞን የአፅቢ ወንበርታ ወረዳ ሓየሎም ቀበሌ ነዋሪ አቶ ርእሶም ሃይሉ ለኢዜአ እንደተናገሩት በየአመቱ የፀረአረም መድሀኒት  ተጠቃሚ አርሶ አደሮች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል።

የጸረ አረም መድሀኒት ተጠቃሚዎች ቁጥር መጨመር ተከትሎ ደግሞ በንብ ማነብ ስራ ለተሰማሩ አርሶ አደሮች ራስ ምታት እንደሆነባቸው ገልጸዋል።

ከአራት አመት በፊት 120 የንብ ቀፎ እንደነበራቸው የተናገሩት አቶ ርእሶም አሁን ላይ በፀረአረም ኬሚካል ምክንያት  ወደ 60 ዝቅ ማለቱን ተናግረዋል።

በገንዘብ ሲሰላ ደግሞ ከ300 ሺህ ብር በላይ ሀብት በመድሀኒቱ ምክንያት እንደወደመባቸው አስረድተዋል።

"ንቦቼ ከመንግስት በተለያየ ወቅት ብድር በማውጣት የተገዙ ናቸው" ያሉት አቶ ርእሶም አሁንም ከ100 ሺህ ብር በላይ ያልተከፈለ እዳ እንዳላባቸው ገልፀዋል።

የንቦቹ ቁጥር መቀነስ ብቻ ሳይሆን በአመት እስከ 7 ኩንታል  ያመርቱት የነበረውን ማር በእጅጉ መቀነሱን ተናግረዋል ።

ከሞትና መጥፋት የተረፉ 60 የንብ መንጋዎችም ቢሆኑ ጤንነታቸው በአስጊ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰው እውቀትና ብልሃቱ ሳይኖራቸው በዘፈቀደ ፀረ አረም ኬሚካል የሚረጩ ሰዎች መንግስት አደብ እንዲገዙ ማድረግ አለበት ብለዋል ።

"ንብ ለማነብ ከሁለት አመት በፊት 13 ቀፎ በመግዛት የጀመርኩት ስራ አሁን መድሀኒቱ ባስከተለው ችግር አምስት መንጋ ብቻ ቀርቷል " ያሉት ደግሞ ሌላው የቀበሌው ነዋሪ  ኮሎኔል አከለን ብርሃን ናቸው ።

የአከባቢው አርሶአደሮች የሚጠቀሙት ፀረአረምና አጠቃቀማቸው ትክክል አይደለም ያሉት ኮሎኔል አከለን አርሶ አደሮቹ  አጠቃቀማቸውና የሚጠቀሙበት ጊዜ እንዲያስተካክሉ ለማስረዳት ቢሞክሩም ፍቃደኛ ባለመሆናቸው ለችግር ተዳርገናል ብለዋል።

አርሶ አደሮቹ የሚጠቀሙት የፀረ አረም  መድሃኒቱ  በኮንትሮባንድ የሚገባ በመሆኑ ለቁጥጥርም አስቸጋሪ ነው ብለዋል።

የፀረ አረም መድሃኒት አጠቃቀማቸው ጠቀሜታውና ጉዳቱ አርሶ አደሮችን ማስረዳት የመንግስት ድርሻ ሊሆን እንደሚገባ ተናግረዋል ።

በወረዳው  ሚካኤል አምባ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አርሶአደር ሻምበል አማረ በበኩላቸው ንቦቹ እያለቁ ያሉት በሚረጨው ፀረአረም መድሀኒት ብቻ ሳይሆን  መዥገር ለመከላከል ሲባል ማላታይን የተባለ መድሀኒት በሚቀቡ  ከብቶች ጭምር ነው ብለዋል።

አርሶ አደሩ እንዳሉት ከ13 የንብ ቆፎ  በዚህ ችግር ምክንያት አራት የንብ መንጋ ብቻ እንደቀሩባቸው ተናግረዋል።

ቀሪዎችም እንቅስቃሴአቸው እየተዳከመ በመሆኑ የመቆየት እድላቸው አጠራጣሪ ነው ብለዋል።

በክልሉ የሚገኝ ግዙፍ የንብ ሀብት ለመታደግ መንግስት በፍጥነት የመፍትሄ ሀሳብ እንዲፈልግ ጠይቀዋል ።

የአርሶ አደሮቹ የፀረአረም መድሃኒት አጠቃቀም ችግር ያለው በመሆኑ በንብ ማነብ ስራ ላይ ለተሰማሩ የክልሉ አርሶ አደሮች ስጋት መጋረጡን  በአካል አረጋግጠናል ያሉት ደግሞ በክልሉ  ግብርና ልማት ቢሮ የንብና አሳ እርባታ ቡድን መሪ አቶ ጎሹ ወልደአብእዝጊ ናቸው።

በንብ መንጋዎች የተጋረጠው አደጋ ለመከላከል ለአርሶ አደሮች የጸረ አረም መድሀኒት አጠቃቀም ግንዛቤ ለመስጠት ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የንብ አርቢዎች መድሀኒት በሚረጭበት ጊዜ ንቦቹ ምግብና ውሃ በማቅረብ አየር በሚያስገባ ቦታ እንዲያስቀምጡ ጭምር ስልጠናው እንደሚሰጥ አስረድተዋል ።

ንብ የሌላቸው አርሶ አደሮች የባለቤትነት ስሜት እንዲሰማቸውና የንብ ባለቤት በማድረግ የመፍትሔው አካል  እንዲሆኑ  እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል ።

እያጋጠመ ያለው አደጋ በህግ ማእቀፍ ለመመለስ የንብ እርባታና ሌሎች ችግሮች የሚቀርፍ  ረቂቅ አዋጅ መዘጋጀቱን አስረድተዋል።

በክልሉ ከ100 ሺህ በላይ አርሶአደሮች በዘርፉ ተሰማርተው እንደሚገኙ ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም