የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን ፕሬዚዳንት ኡርሱላ ቮን ደር ሌይን ነገ አዲስ አበባ ይገባሉ

102

ኢዜአ ህዳር 26 ቀን 2012 የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን ፕሬዚዳንት ሚስ ኡርሱላ ቮን ደር ሌይን በኢትዮጵያ የአንድ ቀን የስራ ጉብኝት ለማድረግ ነገ አዲስ አበባ ይገባሉ።

ሚስ ኡርሱላ ቮን ደር ሌይን ሕዳር 21 ቀን 2012 ዓ.ም የኮሚሽኑ ፕሬዚዳንት ሆነው ከተሾሙ በኋላ በአፍሪካ የሚያደርጉት የመጀመሪያው ጉብኝታቸው ነው።

የኮሚሽኑ ፕሬዚዳንት ጉብኝት ኢትዮጵያና የአውሮፓ ኅብረት ያላቸውን ግንኙነትና ኅብረቱ ለአገሪቷ የሚያደርገውን ድጋፍ ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ለመምከር ያለመ እንደሆነ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ነቢያት ጌታቸው ለኢዜአ ገልጸዋል።

ፕሬዚዳንቷ በኢትዮጵያ ቆይታቸው ከመንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጋር እንደሚወያዩም ተናግረዋል።

በውይይታቸው በኢትዮጵያ እየተካሄዱ የሚገኙ ሁሉን አቀፍ ለውጦችና በቀጣናው ሠላም ዙሪያ ኢትዮጵያ እያከናወነች ያለውን ተግባር አስመልክቶ ማብራሪያ እንደሚደረግላቸውም አመልክተዋል።

የ61 ዓመቷ ፖለቲከኛ በሕዳር 2012 ዓ.ም የኮሚሽኑ ፕሬዚዳንት ሆነው ከተሾሙ በኋላ በአፍሪካ የሚያደርጉት የመጀመሪያ ጉብኝት እንደሆነም ጠቁመዋል።

እ.አ.አ በ1975 የአሁኑ የአውሮፓ ኅብረት የቀድሞ መጠሪያው የአውሮፓ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ከአዳጊ አገራት ጋር የንግድ፣ የኢንዱስትሪና ልማት ትብብር ማጠናከርን ዓላማ በማድረግ የሎሜ ስምምነት መፈራረሙ ይታወሳል።

ከሎሜ ስምምነቱ ፈራሚዎች መካከል ኢትዮጵያ አንዷ እንደነበረችና ከአውሮፓ ኅብረት ጋር ስምምነቱን መሰረት ያደረገ ግንኙነት እንዳላት ነው አቶ ነቢያት የገለጹት።

የአውሮፓ ኀብረት ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር የልዑክ ጽህፈት ቤቱን እ.አ.አ በ1975 እንደከፈተም አስታውሰዋል።

ኢትዮጵያና አውሮፓ ኅብረት የትብብራቸውን ደረጃ ለማሻሻል እ.አ.አ 2016 ስትራቴጂካዊ የሆነ ሁሉን አቀፍ ስምምነት መፈራረማቸውንም አክለዋል።

ስምምነቱ ቀጣናዊ ሠላምና መረጋጋት፣ ሽብርተኝነትና ጽንፈኝነትን መከላከል፣ የስደተኞች ጉዳይ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት፣ ንግድና ኢንቨስትመንት፣ መልካም አስተዳደርና ሰብዓዊ መብት እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥና የከባቢ አየር ትብብር ጉዳዮችን የያዘ ነው።

የአውሮፓ ኅብረት የኢትዮጵያ ዋነኛ አጋር እንደሆነና የኅብረቱ ኮሚሽን ፕሬዚዳንት ኡርሱላ ቮን ደር ሌይን ጉብኝትም ይህንኑ አጋርነት ይበልጥ እንደሚያጠናክረው ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ኅብረት እ.አ.አ 1975 ግንኙነታቸውን ከጀመሩ እስካሁን ኅብረቱ በአገሪቷ ለሚከናወኑ የተለያዩ ስራዎች የ1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዩሮ ድጋፍ ማድረጉን መረጃዎች ያመለክታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም