የአፍሪካና ቻይና የንግድ ልውውጥ ሚዛን መስተካከል አለበት - ዶክተር አርከበ እቁባይ

76

ኢዜአ፤ ህዳር 26/2012 የአፍሪካና የቻይና የንግድ ልውውጥ ሚዛን መስተካከል እንዳለበት የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ ዶክተር አርከበ እቁባይ አስታወቁ።

የአፍሪካና የቻይና የጋራ የቢዝነስ ፎረም በአፍሪካ ህብረት እየተካሄደ ነው።

በጋራ የቢዝነስ ፎረሙ የቻይናና የአፍሪካ ከፍተኛ አመራሮች እስካሁን በነበረው የንግድ፣ ኢንቨስትመንትና ሌሎች ዘርፎች ግንኙነቶች ላይ እየመከሩ ነው።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ ዶክተር አርከበ እቁባይ በመድረኩ ላይ እንደተናገሩት "ቻይና በአሁኑ ወቅት ካሉት የአፍሪካ አጋሮች ዋነኛዋና እስካሁን ለተመዘገበው መልካም እድገትም ትልቅ ሚና ተጫውታለች"።

ያም ሆኖ ቻይና ከአፍሪካ አህጉር ጋር ካላት የባለ ብዙ ዘርፍ ግንኙነት ተጠቃሚ የሆኑት በጣም ጥቂት የአፍሪካ አገራት መሆናቸውን ገልጸው ይህ ዘርፈ ብዙ ጥቅም ወደ ሌሎች አገራትም መስፋት እንዳለበት ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪ የአፍሪካና የቻይና የንግድ ግንኙነት ባለፉት ጥቂት አመታት በ20 እጥፍ ያደገ ቢሆንም ከፍተኛውን ቦታ የያዘው ከአፍሪካ አገራት ወደ ቻይና የሚላከው ምርት ሳይሆን ቻይና ወደ አፍሪካ የምታስገባው ነው ብለዋል።

ይህ ደግሞ ከወጪ ንግድ በላይ የገቢው ንግድ የእድገት ፍጥነት ከፍተኛ መሆኑን እንደሚያሳይና መስተካከል እንዳለበት ነው ያመላከቱት።

የንግድ ሚዛኑ ተስተካክሎ አገራቱ የውጭ ምንዛሬ ማግኘት ካልቻሉ "ቻይና ለአፍሪካ አገራት የምታበድረውን ብድር መክፈልም፣ ከብድሩም መጠቀምም አይችሉም" ሲሉም አስታውቀዋል።

የአፍሪካን መሰረተ ልማት ለማስተካከል በየአመቱ 150 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር እንደሚያስፈልግና ለዚህም የውጭ ንግድን ማጎልበት እንደሚያሻም ተናግረዋል።

በአፍሪካ ህብረት የንግድና ኢንዱስትሪ ኮሚሽን ኮሚሽነር አልበርት ሙቺንጋ በበኩላቸው በአፍሪካና በቻይና መካከል ያለውን የንግድ መዛባት የፈጠረው ቻይና ከፍተኛ የኢንዱስትሪ እድገት ስላመጣችና አፍሪካውያን በኢንዱስትሪ ማስፋፋት ላይ ስላልሰራን ነው" ይላሉ።

በመሆኑም ይህንን ለማስተካከል አፍሪካውያን የምናመርተውን ምርት እሴት ጨምረን ለመላክ የሚያስችል የኢንዱስትሪና የአምራች ዘርፍ ማሳደግ አለብን ሲሉም ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ አፍሪካውያን በተፈጥሮ ማዕድን ወይም በግብርና ላይ ከመወሰን ይልቅ የኢኮኖሚ ዘርፉን ማስፋትና አማራጮችን ማብዛት እንደሚገባም በውይይቱ ላይ ተነስቷል።

በአፍሪካ ህብረት የቻይና ተልዕኮ አምባሳደር ሊዩ ሺ በበኩላቸው አፍሪካ በአሁኑ ወቅት ከሌሎች አህጉራት በላይ ፈጣን እድገት እያስመዘገበች መሆኗንና በተለይም በንግዱ ላይ ትኩረት አድርጋ እየሰራች መሆኗን ጠቅሰዋል።

በአፍሪካና በቻይና መካከል ያለው ግንኙነት ሌሎች አገራት እንደሚሉት "የዘመናዊ ቅኝ ግዛት" መልክ የያዘ ሳይሆን ቀጣይነት ያለው የጋራ እድገት ለማምጣት ነው ሲሉም ተናግረዋል።

በመሆኑም አፍሪካ እየሰራች ያለውን ኢኮኖሚያዊ ተግባር በመደገፍ በኩል ቻይና ምን ጊዜም ወደ ኋላ እንደማትልና በተለይም የሰለጠነ የሰው ሃይል ከማፍራት፣ የገንዘብ ድጋፍና ብድር እንዲሁም የመሰረተ ልማት ግንባታን በተመለከተም ቀጣይ የምናደርጋቸው ድጋፎች ናቸው ነው ያሉት።

የቻይና ባለሃብቶች ወደ አፍሪካ እንዲገቡና መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ በማድረግም የንግድ ሚዛኑ እንዲስተካከል ማድረግ እንደሚቻልም ጠቁመዋል።

ውይይቱ ነገ የሚጠናቀቅ ሲሆን በርካታ በንግድ፣ ኢንቨስትመንትና በሌሎች የኢኮኖሚ ጉዳዮች ዙሪያ ባሉ ችግሮች ላይ መክሮ ውሳኔ ያሳልፋል ተብሎም ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም